ቀጥታ፡

በአሪ ዞን በዘንድሮ የበልግ እርሻ ከ51 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለምቷል

ጂንካ፤ ሚያዚያ 28/2018(ኢዜአ):- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን በዘንድሮ የበልግ እርሻ ከ51 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በተለያዩ ሰብሎች መልማቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።


የመምሪያው ኃላፊ ጉራልቅ ይዥማልቅ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በበልግ አዝመራው እየለማ ካለው መሬት ውስጥ ከ3 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

አርሶ አደሩ ከመደበኛው የሰብል ምርት በተጨማሪ የተሻሻሉ የስንዴ፣ የማሽላ እና የበቆሎ ምርጥ ዘሮችን በኩታገጠም በስፋት በማልማት ለሌሎች አካባቢዎች እያቀረቡ መሆኑንም ገልፀዋል።

ዞኑ የተለያዩ የአየር ፀባዮች ያለው በመሆኑም በተለይ በደጋው አካባቢ ስንዴ፣ ገብስ፣ ባቄላ እና አተር እየተመረተ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ወይናደጋ እና ቆላማ በሆኑት አካባቢዎች ደግሞ ጤፍ፣ ማሽላ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ ለውዝ፣ ሰሊጥ፣ ማሾ እና መሰል ሰብሎች በስፋት እየለማ መሆኑንም አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ምርታማነቱን እንዲያሻሽል በማሰልጠኛ ማዕከላት ተግባር ተኮር ትምህርት እየተሰጠ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ የባካ ዳውላ አሪ ወረዳ አርሶ አደር ማርቆስ አዲሱ፥ በዘንድሮው የበልግ አዝመራ በቆሎና በአጭር ጊዜ የሚደርሱ የጓሮ አትክልቶችንም በማልማት የገቢ አቅማቸውን ማሳደጋቸውን ነው የሚገልጹት።

ሌላው አርሶ አደር ግርማ ከማይ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የበልግ አዝመራ ከሌሎች አርሶ አደሮች ጋር በመጣመር በ10 ሄክታር መሬት ላይ በኩታ ገጠም ስንዴ እያለሙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ከጥቂት ጊዜ ወዲህ የስንዴ ምርት በኢንዱስትሪውም ሆነ በማሕበሩ በስፋት የሚፈለግ በመሆኑ በዘርፉ መስራታቸው ውጤታማ እያደረጋቸው መምጣቱን ጠቁመዋል።

ከግብርና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ምክረ ሀሳቦች በመተግበራቸውም ምርትና ምርታማነታቸውን እንዳሳደገላቸው ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም