ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የሚቲዎሮሎጂ ዘርፍን ለማዘምን ያከናወነቻቸው ተግባራት አርዓያ የሚሆኑ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የሚቲዎሮሎጂ ዘርፍን ለማዘምን ያከናወነቻቸው ተግባራት አርዓያ የሚሆኑ ናቸው
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የሚቲዎሮሎጂ ዘርፍን ለማዘመን ያከናወነቻቸው ውጤታማ ስራዎች የአፍሪካን አቅም የሚያሳድጉ መሆናቸውን ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የተውጣጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ከአፍሪካ ሜቲዎሮሎጂ ሶሳይቲ ጋር በመተባበር የመጀመሪያውን ሳይንቲፊክ ኮንፍረንስ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
በኮንፍረንሱ የተሳተፉ ባለሙያዎች እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም፣ በሚቲዎሮሎጂ እንዲሁም በሃይድሮሎጂ ምልከታዎች ዙሪያ በጋራ መሥራታቸው ወሳኝ ነው።
ይህም የተፈጥሮ አደጋዎች ሳይከሰቱ አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስችሉ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስልቶችን ለማጎልበት እንደሚረዳ አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ በዘርፉ ላከናወነቻቸው የቴክኖሎጂና የመሠረተ ልማት ኢንቨስትመንቶች አድናቆታቸውን ገልጸው፤ እነዚህ ኢንቨስትመንቶች ከኢትዮጵያ አልፈው ለአህጉራዊ የኢኮኖሚ ትስስርና የመቋቋም አቅምን ለመገንባት ትልቅ ድርሻ አላቸው ብለዋል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ፣ የታዳሽ ኃይልን ከማስፋፋት እና በሌሎች የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም በሚያስችሉ ተግባራት ዙሪያ ያሳየችው ውጤት የመንግስትን ቁርጠኝነት በተግባር የሚያመላክት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚምባቡዌ የመጡት ፍሪዶ ሙካንጋ በሰጡት አስተያየት፤ በኢትዮጵያ የሚቲዎሮሎጂ ዘርፍን ለማዘመንና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እጅግ የሚያስደንቁና ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተነሳሽነትን የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
ኢንስቲትዩቱ በመረጃ አያያዝና በከፍተኛ አቅም በሚሰሩ የኮምፒውተር ቴክኖሎጂዎች ላይ ያደረገው ኢንቨስትመንት መንግሥት ለዜጎቹ ሕይወት መታደግ ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሥነ-ምሕዳርን ከመጠበቅ ባለፈ ለምግብነት የሚውሉ ተክሎች ላይ ትኩረት ማድረጉ፣ ለዜጎች የገቢ ምንጭ እንዲሆንና ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ማስቻሉን ገልጸዋል።
በሃይድሮሎጂ ዘርፍ የሚደረጉ ምልከታዎችና ጥናቶችም ለኃይል ማመንጫ፣ ለመስኖ ልማትና ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ዕድገት የጀርባ አጥንት ለሆኑ ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ እገዛ እያደረጉ መሆኑን መረዳታቸው ጠቅሰዋል፡፡
የታንዛንያው ተወካይ ዶክተር ፍሬድበሪት ኦዱንጋ በበኩላቸው፤ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽዕኖን የመቋቋም አቅሟን ለማጎልበት ሀገራት በጋራ መሥራት፣ ግብዓቶችን መጋራት እና የተቀናጁ ስልቶችን መቅረጽ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ በውኃ አስተዳደር እና በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ግንባታ ላይ ያከናወነቻቸው ተግባራት ለአህጉራዊ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋም ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በመሠረተ ልማት ዘርፍ እያከናወነች ያለችው ሰፊ ጥረት ለመላው አፍሪካ የመቋቋም አቅም መጎልበት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ኬንያዊቷ ማሪያ ሎኪ ቻሬም በበኩላቸው የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸውን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በበለጠ ፍጥነትና ውጤታማነት ለመፍታት የአፍሪካ ሀገራት በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ ተሞክሮ ለሌሎች ሀገራት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከኢትዮጵያ ልምድ በመነሳት የአፍሪካ ሀገራት ለአህጉሪቱ ስኬት መሥራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል፡፡