በዞኑ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ39 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ39 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል
ደሴ፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ39 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የተፈጥሮ ሀብት ልማት፣ ጥበቃና አጠቃቀም ቡድን መሪ መገርሳ ተሾመ ለኢዜአ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ በተተከሉ ችግኞች ተጨባጭ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
የደን ሽፋንን በማሳደግ፣ በተፋሰሶች በእንሰሳት መኖ፣ በንብ ማነብ፣ በፍራፍሬ ልማትና በሌሎችም ለወጣቱ የሥራ እድል በመፍጠር እንዲሁም የሰብል ምርታማነትን በማሳደግ አበረታች ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል በዘንድሮ ክረምት በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርህ ግብር ከ39 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ችግኝ ለመትከል ዝግጅት መደረጉንና ለዚህም የችግኝ ዝግጅት መከናወኑን ተናግረዋል።
የደሴ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር አደም ከድር በሰጡት አስተያየት በየአመቱ ችግኞችን በማፍላት በራሳቸው መሬት በመትከልና የተረፈውን በመሸጥ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በቃሉ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አህመድ መሀመድ በበኩሉ በያዝነው በጋ ከ100 ሺህ በላይ የማንጎ፣ ቡና፣ አቡካዶና ሌሎች የፍራፍሬ ችግኞች ማዘጋጀቱንና በመጭው ክረምት በመሸጥ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እየሰራ መሆኑን አመላክቷል።
በደቡብ ወሎ ዞን ባለፈው ክረምት ከተተከለው 210 ሚሊየን ችግኝ መካከል ከ75 በመቶ በላይ መጽደቁን ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡