ቀጥታ፡

የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ መድን ጋር የሚያደርጉት ተጠባቂ ፍልሚያ

አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ፍጻሜውን ያገኛል።

በዕለቱ ከሚከናወኑ ጨዋታዎች መካከል ሲዳማ ቡና ከ ኢትዮጵያ መድን የሚያደርጉት ጨዋታ ተጠቃሽ ሲሆን፤ ግጥሚያውም በአዲስ አበባ ስታዲየም ዘጠኝ ሰዓት ላይ ይጀምራል።

ሲዳማ ቡና በ55 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው። ተጋጣሚው ኢትዮጵያ መድን በ35 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሊጉን እየመራ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በ29ኛ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል። 

የወቅቱ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ኢትዮጵያ መድን ካለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። 

ሲዳማ ቡና መሪነቱን ለማጠናከር፣ ኢትዮጵያ መድን ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ርቆ ደረጃውን ለማሻሻል የሚያደርጉት ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ክለቦች ወሳኝ የሚባል ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ የመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።

በሌላኛው መርሐ ግብር ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከነገሌ አርሲ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ35 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው ነገሌ አርሲ በ45 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ባለፉት ሁለት የሊግ ጨዋታዎች ድል የቀናው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠና ስፍራ ለመራቅ የሚያስችለውን ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።

አዲስ አዳጊው ነገሌ አርሲ ባለፉት አራት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል። ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል። 

ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ ፋሲል ከነማ ከባህር ዳር ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ፋሲል ከነማ በ43 ነጥብ አምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ባህር ዳር ከተማ በ37 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል።

ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ ማግኘት ያልቻለው ፋሲል ከነማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።

ባህር ዳር ከተማ በዘንድሮው ውድድር ካደረጋቸው ጨዋታዎች መካከል 16 ጊዜ በአቻ ውጤት በመጨረስ በሊጉ ቀዳሚው ነው። ባለፉት ሶስት ጨዋታዎችም ድል አልቀናውም።

ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይፋለማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም