ቀጥታ፡

በጅማ ዞን ለዘንድሮው የአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ዝግጁ ሆነዋል

ጅማ፤ ሚያዝያ 28/2018(ኢዜአ)፦ በጅማ ዞን ለዘንድሮው የአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ዝግጁ መደረጋቸውን የዞኑ ግብርና ፅህፈት ቤት አስታወቀ።

የጅማ ዞን ግብርና ፅህፈት ቤት ሃላፊ ቲጃኒ ተማም፤ ለደን ልማት፣ ለፍራፍሬ፣ ለውበትና የእንስሳት መኖን ጨምሮ ሌሎችንም ባካተተ መልኩ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም 91 ሺህ ሄክታር መሬት ለችግኝ መትከያ የተዘጋጀ መሆኑንና ለስኬታማነቱ ከወዲሁ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ለልማቱ የችግኝ ዝግጅት ከማድረግ በተጓዳኝ ከዚህ ቀደም የተተከሉትን የመንከባከብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው ዘንደሮም በተጠናከረ መልኩ የሚቀጥል መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ቀርሳ ወረዳ አርሶ አደር ሙላቱ ደበሌ እና አርሶ አደር ቲጃኒ አባ ጎጀም፤ የሚተከሉ ችግኞች ለምግብ ዋስትና መሰረት እየሆኑ በተግባር እየተጠቀምንባቸው እንገኛለን ብለዋል።

ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለእንስሳት መኖ እና ምቹ የመኖሪያ አካባቢ ለመፍጠር የሚተከሉ ችግኞች ትልቅ ትርጉም እንዳላቸውም አንስተዋል።

በመሆኑም የተተከሉትን ችግኞች በመንከባከብና የተራቆቱ አካባቢዎችን በዛፍ በመሸፈን የበኩላችንን እንወጣለን ነው ያሉት።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር በንቃት ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውንም አርሶ አደሮቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ አቅምን ለመገንባት ትልቅ አቅም የሆነ ኢንሼቲቭ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም