የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ድግስ፦ ባየር ሙኒክ ከ ፒኤስጂ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ ድግስ፦ ባየር ሙኒክ ከ ፒኤስጂ
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 28/2018 (ኢዜአ)፦ ባየር ሙኒክ ከፒኤስጂ ዛሬ የሚያደርጉት የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ በእግር ኳስ አፍቃሪያን ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል።
ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በአሊያንዝ አሬና ስታዲየም ይጫወታሉ።
ሁለቱ የአውሮፓ ኃያላን ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ፒኤስጂ 5 ለ 4 አሸንፏል።
ማራኪ፣ አዝናኛ እና በማጥቃት ላይ የተመሰረተው የመጀመሪያው ጨዋታ በእግር ኳስ ቤተሰቡ አድናቆት ተችሮታል።
ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምንጊዜም ምርጥ ጨዋታዎች አንዱ እና ከፍጻሜው በፊት የፍጻሜ ጨዋታ የሚል ስያሜም በብዙዎች ዘንድ ተሰጥቶታል።
ሁለቱም ክለቦች ለዛሬው ጨዋታ ማጥቃትን ቀዳሚ መመሪያቸው አድርገው ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ከቡድኖቹ ካምፕ ተሰምቷል።
የቡድኖቹ የማጥቃት ጠንካራ ፍላጎት ለእግር ኳስ አፍቃሪያን መልካም ዜና ነው።
የስድስት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ባየር ሙኒክ ለፍጻሜው ለማለፍ ይጫወታል።
የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ፒኤስጂ ክብሩን በማስጠበቅ ጉዞው ለመቀጠል ጠንካራ ፈተና ከጀርመኑ ክለብ ይጠብቀዋል።
እግር ኳስ አፍቃሪያን እንደ መጀመሪያው ዙር ሁሉ በዛሬውም ጨዋታ በቴሌቪዥን መስኮታቸው ማራኪ ፉክክርን ለመመልከት በጉጉት ይጠብቃሉ።
የ38 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ ጆአኦ ፒንሄሮ ተጠባቂውን ፍልሚያ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።
የሁለቱ ቡድኖች አሸናፊ በፍጻሜው ከአርሰናል ጋር ይገናኛል።
ትናንት በተደረገ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ አርሰናል አትሌቲኮ ማድሪድን 1 ለ 0 በድምር ውጤት 2 ለ 1 በማሸነፍ ለፍጻሜ አልፏል።