አርሰናል ከ20 ዓመታት በኋላ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ አለፈ - ኢዜአ አማርኛ
አርሰናል ከ20 ዓመታት በኋላ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ አለፈ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ አርሰናል አትሌቲኮ ማድሪድን 1 ለ 0 አሸንፏል።
ማምሻውን በኤምሬትስ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ቡካዮ ሳካ በ44ኛው ደቂቃ የማሸነፊያውን ጎል አስቆጥሯል።
ግልጽ የግብ እድሎች ውስን በነበሩበት ጨዋታ አርሰናል በመጀመሪያ አጋማሽ ያገኘውን መሪነት አስጠብቆ ወጥቷል።
ውጤቱን ተከትሎ አርሰናል በድምር ውጤት 2 ለ 1 በማሸነፍ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ አልፏል።
መድፈኞቹ ለመጨረሻ ጊዜ ለፍጻሜ ያለፉት እ.አ.አ በ2006 ነበር። ለፍጻሜ ሲያልፉ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
አርሰናል በዘንድሮው ሻምፒዮንስ ሊግ ምንም ጨዋታ ሳይሸነፍ ለፍጻሜ ደርሷል።
14 ጨዋታዎቹን አድርጎ 11ዱን ሲያሸንፍ በሶስቱ አቻ ወጥቷል።
አርሰናል በፍጻሜው ከባየር ሙኒክ እና ፒኤስጂ አሸናፊ ጋር ግንቦት 22 ቀን 2018 ዓ.ም በቡዳፔስት ይጫወታል።
አትሌቲኮ ማድሪድ ከ10 ዓመታት በኋላ ለሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ የማለፍ ህልሙ አልተሳካም።
የባየር ሙኒክ እና ፒኤስጂ የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ነገ ይደረጋል።