ቀጥታ፡

ጉባዔው የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የአፍሪካውያንን አጀንዳ ለማስረፅና የጋራ ድምፅን ለማሰማት ዕድል ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካ ማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባዔ (ASMIS) የአፍሪካውያንን አጀንዳ ለማስረፅና የጋራ ድምፅን ለማሰማት ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የፐልስ ኦፍ አፍሪካ አስተባባሪ አቶ በረከት ሲሳይ ገለጹ።

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa-POA) ከ ኤ.ጂ.ኤ የቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ (AGA-Tech) ጋር በመተባበር "ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ለተሻለች አፍሪካ" በሚል መሪ ሐሳብ የሚያዘጋጀው ይህ ጉባዔ፤ ሚያዚያ 29 እና 30 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ በዓድዋ ድል መታሰቢያ ይካሄዳል።

ጉባዔው ኃላፊነት የሚሰማቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችን ለማበረታታት፣ ዲጂታል ኢኮኖሚን ለማጠናከር፣ ትብብርን ለመፍጠርና የዲጂታል ማዕከል ለማድረግ ያለመ ነው። 

የጉባዔው አዘጋጆችም፤ የኢትዮጵያ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በጉባዔው ወቅት የሀገራቸውን ገጽታ መገንባትና ትብብራቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።


 

የፐልስ ኦፍ አፍሪካ አስተባባሪ አቶ በረከት ሲሳይ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የአፍሪካን የተዛባ ትርክት ለመቀየር የተመሠረተ የፓን አፍሪካ ሚዲያ ነው።

ጉባዔው ከኤ.ጂ.ኤ ቴክኖሎጂ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ "የአፍሪካን ትርክት በራሳችን ሰዎች መናገር አለብን" የሚለውን መርኅ ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

የጉባዔው ዋነኛ ዓላማም በተፅዕኖ ፈጣሪዎች መካከል ጠንካራ ትብብር በመፍጠር በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የጋራ ድምጽ ማሰማት የሚችሉበትን ዕድል ማመቻቸት እንደሆነ አመላክተዋል።

የአፍሪካ ኅብረት አጀንዳ 2063 አህጉሪቷ የምትመራበት የ50 ዓመት ዕቅድ መሆኑን የጠቀሱት አስተባባሪው፤ በሕዝቦች መካከል የጋራ መግባባት ለመፍጠር የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በጋራ የሚሠሩበትን ዕድል ለመፍጠር መድረኩ ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል።

ስለሆነም ጉባዔው አፍሪካውያን የአጀንዳውን ግቦች ለማሳካት በጋራ የሚሠሩበት መድረክ ይሆናል ብለዋል።

ዲጂታል ሚዲያ የኢኮኖሚ ማንቀሳቀሻ ትልቅ መድረክ ነው ያሉት አቶ በረከት፤ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ማኅበራዊ ሚዲያውን ማኅበረሰቡን በሚጠቅም መንገድ እንዲጠቀሙበት የጋራ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።


 

የኤ.ጂ.ኤ. ቴክ ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ገመዳ ኦላና በበኩላቸው፤ ጉባዔው የኢትዮጵያን ብሎም የአፍሪካን ገፅታ ለመገንባት ወሳኝ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል። 

የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ስለ ይዘት ፈጠራ፣ ስለ አፍሪካ ትርክት ግንባታና ስለ አጀንዳ 2063 ግቦች ግልጽ አቋም እንዲይዙ ያስችላል ብለዋል።

ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ለጉባዔው የተመረጡ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች፤ በማኅበራዊ ሚዲያ ያላቸው ተደራሽነትና የአፍሪካን ገጽታ ለመገንባት በሚኖራቸው አስተዋጽኦ ተመዝነው የተመረጡ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም