ቀጥታ፡

የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባዔ የአፍሪካን ትክክለኛ ገጽታ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ ያስችላል

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፡-የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባዔ (ASMIS-2026) የአፍሪካን ትክክለኛ ገፅታ ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ማስተዋወቅ የሚያስችል መድረክ መሆኑን የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ገለፁ።


 

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (Pulse of Africa-POA) እና ኤጂኤ ቴክ (AGA-Tech) በጋራ ያዘጋጁት የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባዔ (ASMIS-2026) ሚያዝያ 29 እና 30 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

በዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄደው ይህ አኅጉራዊ መድረክ፤ አፍሪካ በዲጂታሉ ዓለም ያላትን ድምፅ ለማጉላትና ትክክለኛውን የአፍሪካ ትርክት ለዓለም ለማስተዋወቅ ያለመ ነው።

የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባዔ፤በተፅዕኖ ፈጣሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣በአፍሪካ ዳያስፖራዎችና በግሉ ዘርፍ ተዋናዮች መካከል የረጅም ጊዜ ትብብር የሚፈጠርበት ነው፡፡

የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የቅድመ-ጉባዔ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ የማኅበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያን ጎብኝተዋል።


 

በዚህ ወቅት የአላይቭ ፖድካስትና ካምፓኒ ሥራ አስኪያጅ አብርሃም ፋንቱ እንዳለው፤ የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጠራ የማኅበረሰብን ንቃተ-ኅሊና የመቀየርና የሰዎችን አስተሳሰብ የመቅረፅ ዐቅም አለው።

የአፍሪካ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ጉባዔ በርካታ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ገልጾ፤ የይዘት ሥራችንን ከሀገር አልፎ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብሏል።

ጉባዔው ኢትዮጵያ ያላትን ሀብት የበለጠ ለማስተዋወቅና የአፍሪካን ትክክለኛ ገፅታ ለዓለም ለማሳየት የሚረዳ መሆኑንም ተናግሯል።


 

የዳሎል ኢንተርቴይመንት፣ዳሎል ገበያና ዳሎል አካዳሚ መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ጢሞቲዮስ ዘካሪያስ በበኩሉ፤ጉባዔው የማኅበራዊ ሚዲያ ይዘት ፈጣሪዎች ለሀገራቸው አስተዋፅኦ ለማበርከት የሚያስችል ነው ብሏል።

ማኅበራዊ ሚዲያ ለአፍሪካ ከማዕድን በላይ የሆነ ሀብት ነው ያለው ዶክተር ጢሞቲዮስ፤ ጉባዔው ዓለም ስለ አፍሪካ ያለውን የተዛባ አረዳድ ለማስተካከል የሚረዳና ለገፅታ ግንባታ የጎላ ሚና ያለው መድረክ መሆኑን ተናግሯል።

አፍሪካ በአፍሪካውያን መወከልና መገለፅ አለባት ያሉት የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎቹ፤ የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ የአፍሪካን ድምፅ ለማንፀባረቅና ለማሳየት የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበል።

በጉብኝታቸውም ፐልስ ኦፍ አፍሪካ በብቁ ባለሙያዎች፣ በዘመናዊ መሳሪያና አሠራር የተደራጀ፣ የአፍሪካን ትክክለኛ እውነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማሰማት የሚያስችል ትልቅ ዐቅም ያለው ሚዲያ መሆኑን ተመልክተናል ብለዋል።

#Ethiopian_News_Agency #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም