ቀጥታ፡

በኪነ-ጥበብ ዘርፍ የላቀ ዐሻራ ላበረከቱ ሙያተኞች ክብር መሰጠቱ ተገቢ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፡- በኪነ-ጥበብ ዘርፍ ለሀገር የላቀ ዐሻራ ላበረከቱ ሙያተኞች ተገቢው ክብር በመሰጠቱ ደስታ ተሰምቶናል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው በአዲስ አበባ የሚገኙ የኪነ-ጥበብ ቤተሰቦች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያን በጥበብ ሙያቸው ላገለገሉ የሀገር ባለውለታዎች የተሠሩ የመታሰቢያ ሐውልቶችን ዛሬ መርቀዋል፡፡
 
ከምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ጥበብ ሀገር ትሠራለች፤ ሀገርም ጠቢብን ታከብራለች ብለዋል። 
 
የሀገር ባለውለታ ለሆኑና በጥበብ ሙያቸው ለሀገራችን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ባለሙያዎች በከተማችን የመታሰቢያ ሐውልቶች ቆሞላቸዋል ሲሉ ገልጸዋል።
 
የኪነ-ጥበብ ሙያተኞች ለሀገር ካበረከቱት አስተዋጽኦ አኳያ የሚዘከሩበት ሐውልት መቆሙን በተመለከተ የኪነ-ጥበብ ቤተሰቦችን አነጋግረናል። 

 
 

የአንጋፋው አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ ባለቤት ወይዘሮ ሮማን በዙ እንደገለጹት፤ ባለቤታቸው በሙዚቃው መስክ ለሀገሩ ለሠራው ሥራ ክብር ለመስጠት ሐውልት በመቆሙ ልዩ ስሜት ተሰምቷቸዋል። 
 
አሁን ለተሠራው ሥራና መንግሥት ላበረከተው አስተዋጽኦ በቤተሰባቸው ስም ምሥጋና አቅርበዋል።
 
አርቲስት ጥላሁን እና ሌሎች በኪነ-ጥበብ መስክ ዕድገት ላይ የራሳቸውን ሚና የተጫወቱ አንጋፋ ሙያተኞችን ሀገር ስታከብራቸው ማየት ኩራት መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ተግባር የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ‘እኔም ለሀገሬ መልካም ከሠራሁ ታሪኬ ይዘክረኛል’ የሚል አስተሳሰብ ኖሮት እንዲሠራ ያበረታታል ብለዋል።

 
 

አርቲስት ነዋይ ደበበ በበኩሉ፤ በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች ላይ ለሚገኙ እንቁ ሙያተኞች መንግሥት ለሰጠው ክብር አመሥግኗል። 
 
ለአንጋፋ አርቲስቶቹ ሐውልት ማቆም ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ማድረግ መሆኑንም ገልጿል።


 

ለሀገርና ለኪነ-ጥበብ ዕድገት አስተዋጽኦ ያደረጉ ሙያተኞችን የሚዘክር ሐውልት ማስቀመጥ ያልተለመደ መሆኑን የተናገረው ደግሞ አርቲስት ኤልያስ ተባባል ነው። 
 
ዛሬ ላይ በሕይወት ላሉም ለሌሉም አንጋፋ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ለሠራው ሥራ ዕውቅና የሚሰጡ መታሰቢያዎች በመቆማቸው ደስታ ተሰምቶኛል ብሏል። 
 
አርቲስቶች የሠሩትን ሥራ የሚዘክሩ ምልክቶች ሲቀመጡ፤ ትውልዱ ኢትዮጵያ ለሙያተኞች የምትሰጠውን ክብር በአግባቡ እንዲገነዘብ ያደርጋል ሲልም አክሏል።

 

ኪነ-ጥበብን ለማሳደግ የመንግሥት ድጋፍና ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ያስገነዘበው ደግሞ አርቲስት ዘለቀ ገሰሰ ነው።

መንግሥት ለኪነ-ጥበብ ሙያ እየሰጠ ያለው ዕውቅና የሚበረታታ መሆኑንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም