ኢትዮጵያ በዘመናዊ ወታደራዊ ጥበብና በላቀ ሥነ-ልቦና የታነጸ ሠራዊት ገንብታለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በዘመናዊ ወታደራዊ ጥበብና በላቀ ሥነ-ልቦና የታነጸ ሠራዊት ገንብታለች
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ) ፦ ኢትዮጵያ በዘመናዊ ወታደራዊ ጥበብ፣ በላቀ ሥነ-ልቦና የታነጸና ጥቃትን በብቃት መመከት የሚችል ሠራዊት መገንባቷን የባሕር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ ገለጹ።
85ኛው የድል በዓል በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሐውልት አደባባይ ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትን ጨምሮ አባትና እናት አርበኞች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አዛዥ ቫይስ አድሚራል ክንዱ ገዙ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ጀግንነት የኢትዮጵያውያን መታወቂያና የነፃነታቸው ዋስትና ነው።
ኢትዮጵያ በረጅም ዘመናት ታሪኳ በልጆቿ መስዋዕትነት የነፃነትና የታላቅነት የድል ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል።
ከዘመኑ ጋር የሚራመድ ወታደራዊ ጥበብን በመተግበር፣ ከጠላት በላይ በገነቡት አቅምና ብቃት የወራሪዎችን ሕልም በማክሸፍ ደማቅ ታሪክ መጻፍ መቻሉንም ተናግረዋል።
የድል በዓሉም በኢትዮጵያ የታሪክ ገጾች ውስጥ በደማቅ ቀለም የተጻፈ፣ በሀገሪቷ የአምስት ዓመት የአርበኝነት ትግል ጊዜ አልፎ ዳግም የነፃነት ብርሃን የበራበት መሆኑን ገልጸዋል።
አርበኞች ወራሪ ኃይሉን መስዋዕትነት ከፍለው በማሸነፍ፣ አይበገሬነታቸውን ለዓለም በተግባር ያረጋገጡበት ዕለት መሆኑንም አውስተዋል።
አባቶቻችን በኢትዮጵያ የአንድነት ጥላ ሥር በጋራ ተሰልፈው ጠላትን ድል እንዳደረጉ፤ ዛሬም ለሀገር ሕልውናና ሉዓላዊነት መከበር በአንድነትና በመተባበር ሁሉም ዜጋ ሊረባረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ትውልዱ እንደ ሀገር ያሉብንን ፈተናዎች በጽናት ለመሻገር፣ እንደ አባቶቹ የጸና አንድነትና የሀገር ፍቅር ስሜት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፋዊና ወቅታዊ ሁኔታዎችን ያገናዘበ፣ በቀጣናው ያንዣበቡ ሥጋቶችን መቀልበስ ብሎም ተጨማሪ ተልዕኮዎችን መፈጸም የሚያስችል ያልተቋረጠ የዝግጁነት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በግፍ ያጣነውን የባሕር በር ለማስመለስ መንግሥት የሚያደርገውን ዘርፈ ብዙ ጥረት ለመደገፍ፣ ጠንካራ የባሕር ኃይል እየተገነባ መሆኑንም ገልጸዋል።