ቀጥታ፡

ድህነትና ኋላቀርነትን ታግሎ ማሸነፍና ለሀገር አንድነት ዘብ መቆም ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ ድህነትና ኋላቀርነትን ታግሎ ማሸነፍና ለሀገር አንድነት ዘብ መቆም ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት መሆኑን የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ገለጹ።

85ኛው የድል በዓል በአዲስ አበባ አራት ኪሎ በሚገኘው የድል ሐውልት አደባባይ ተከብሯል።


 

በበዓሉ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላትን ጨምሮ አባትና እናት አርበኞች ተገኝተዋል።   

የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን በዚሁ ወቅት፤ ከ85 ዓመት በፊት የህይወት መስዋዕትነትን የከፈሉ አርበኞች ሉዓላዊነቷ የተጠበቀ ነፃ ሀገር እንድንረከብ አድርገዋል ብለዋል።

ከ85 ዓመት በፊት ለአምስት ዓመታት መራር የሆነ የግፍ ፅዋ ተጎንጭተው ሀገርን ለታደጉ አርበኞች ምስጋና፣ ፍቅርና አክብሮት ይገባልም ብለዋል።  


 

ዛሬም ሀገሪቱ ድህነትንና ኋላቀርነትን ታግለው የሚያሸንፉ፣ የልማት እንዲሁም ለሀገር አንድነትና ለህዝብ ፍቅር ዘብ የሚቆሙ የወቅቱ አርበኞች ያስፈልጋታል ብለዋል፡፡   

ድህነትና ኋላቀርነትን ታግሎ ማሸነፍና ለሀገር አንድነት ዘብ መቆም ዘመኑ የሚጠይቀው አርበኝነት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡   

በሀገሪቱ ታሪክ አዲስ የሆነው ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የሚያስችለውን ሀገራዊ ምክክር መድረክ ይዞ የመጣውን እድል መጠቀም ይገባልም ብለዋል።


  

ፍትሃዊ ባልሆነ አግባብ ያጣነውን የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የህልውናና የመብት ጉዳይ መሆኑን መረዳት እንደሚገባም ተናግረዋል።   

አባቶቻችን ከጠላት በትንቅንቅ ሲፋለሙ የነበረው ለግል ጥቅማቸው ሳይሆን ለሀገር ነፃነትና ሉዓላዊነት እንደነበር አውስተው ወጣቱ ትውልድ ታሪክን አውቆ ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም