ትውልዱ ከነጠላ ትርክት ይልቅ በአሰባሳቢ ትርክቶች ላይ ማተኮር ይገባዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
ትውልዱ ከነጠላ ትርክት ይልቅ በአሰባሳቢ ትርክቶች ላይ ማተኮር ይገባዋል - ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ ትውልዱ ከታላላቅ የጥበብ ሰዎች ትምህርት በመውሰድ ከነጠላ ትርክት ይልቅ በአሰባሳቢ ትርክቶች ላይ ማተኮር እንደሚገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኢትዮጵያን በጥበብ ሙያቸው ላገለገሉ የሀገር ባለውለታዎች የተሠራውን የመታሰቢያ ሐውልት መርቀዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ሐውልቱ የቆመው የጥበብ ሰዎች ሀገርን ለመገንባት ላደረጉት አስተዋጽኦ የላቀ ክብር ምስክርነት ለመስጠት ነው፡፡
የጥበብ ሰዎች ለሀገር ግንባታ፣ ለሕብረ-ብሔራዊ አንድነት፣ ለእኩልነትና ለነፃነት በሙያቸው ትልቅ ዋጋ የከፈሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጥበብ ሰው አካላዊ ሕይወቱ ቢያልፍም የሠራቸው ሥራዎች ግን እንደ ፀሐይ እየደመቁ ለዘላለም ይኖራሉ ብለዋል።
ሐውልቱ ከተማዋ የባህል ማንነቷን እንድትገልጽ ከማድረጉም በላይ፣ የአዲስ አበባን ውበት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል።
ትውልዱ ከታላላቅ የጥበብ ሰዎች ትምህርት በመውሰድ ከነጠላ ትርክት ይልቅ አሰባሳቢ ትርክት ላይ ማተኮር እንዳለበት አሳስበዋል።
ማኅበረሰብን ከሚያራርቁ ነጠላ ትርክቶች በመውጣት ሁሉንም አቃፊና አስተሳሳሪ የወል ትርክት መገንባት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የሀገር ባለውለታዎችን መዘከርና ማስታወስ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ እንዳልሆነ የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ መሰል የክብር መገለጫዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ በበኩላቸው የጥበብ ሰዎችን በአደባባይ ከፍ አድርጎ መዘከር ለሙያውና ለባለሙያዎች የተሰጠ ትልቅ ክብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የጥበብ ሰዎች ትውልድን በማስተሳሰርና ሀገርን በመገንባት የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸው፤ በድንቅ ሥራዎቻቸው ሁሌም በሕዝብ ልብ ውስጥ ዘላለማዊ ናቸው ብለዋል፡፡