የኮሪደርና የቱሪስት መዳረሻ ልማት ስራዎች ከተሞችን ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ዕድሎችን አምጥተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደርና የቱሪስት መዳረሻ ልማት ስራዎች ከተሞችን ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ዕድሎችን አምጥተዋል
ሀዋሳ ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደርና የቱሪስት መዳረሻ ልማት ስራዎች ከተሞችን ለኑሮ ምቹ ከማድረግ ባለፈ ዘርፈ ብዙ ዕድሎችን ይዘው መምጣታቸውን ምሁራን ገለጹ።
"በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቱሪዝም ልማት ውስጥ ፈጠራና ዘላቂነት" በሚል መሪ ሀሳብ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው 15ኛው ሀገር አቀፍ የምርምር ኮንፈረንስና የኮሪደር ልማት የልምድ ልውውጥ መድረክ መካሄዱ ይታወሳል።
በወቅቱም ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራን እንደገለጹት፤ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ በመቀየር ውብና ማራኪ ከማድረግ ባለፈ የቱሪስት ቆይታን በማራዘም ዘርፈ ብዙ ዕድሎችን ይዞ መጥቷል።
በኢትዮጵያ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደርና የመዳረሻ ልማት ስራዎች የቱሪስትን ቆይታ ከማራዘም ባለፈ ለከተማ ነዋሪው ምቹ የመዝናኛ አማራጭ ይዞ መምጣቱን ነው ምሁራኑ የተናገሩት።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስትራቴጂ ፕሮግራሞች ማኔጅመንት ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር እሸታየሁ ክንፉ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ከተሞች ያላቸውን ጸጋ ለይተው የሚያለሟቸው የመዳረሻ ልማት ስራዎች በርካታ ጠቀሜታዎችን ይዘው መጥተዋል።
በመላ ሀገሪቱ ከተሞችን ለማዘመንና ምቹ የመኖሪያ፣ የስራና የቱሪስት ማዕከል ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደርና የመዳረሻ ልማት ስራዎች ለነዋሪው ምቹ የመዝናኛ አማራጭና ጎብኚዎች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ ለማድረግ አስችሏል ብለዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ኢኒሼቲቭ አዲስ አበባ ላይ የተከናወኑ የኮሪደርና የመዳረሻ ስፍራዎች ልማት ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው ይህም የከተማዋን ተመራጭነት በማሳደግ ለገቢ ማደግም የበኩሉን ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት።
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዚዳንት ታፈሰ ማቲዮስ (ዶ/ር)፤ በሀዋሳ ከኮሪደር ልማት ስራው በተጓዳኝ የሀይቅ ዳርቻ ልማት ስራውን ዩኒቨርሲቲው በአማካሪነት እያገዘ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የሀይቅ ዳርቻ ልማቱ ደረጃውን የጠበቀ በአካባቢው ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ባማከለ መልኩ የሚሰራ በመሆኑ ከተማዋን በአዲስ ገጽታ፣ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ እንደከተታት ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ተባባሪ ፕሮፌሰር ምህረት ደናንቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የከተሞችን ውበት የጨመረው የኮሪደር ልማት ስራ የመዝናኛና የገቢ ማግኛም ጭምር ዕድልን ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል።
የከተማዋ ግርማ ሞገስ የሆነው የሀዋሳ ሀይቅን በተገቢው ለመጠቀም የተጀመረው የሀይቅ ዳርቻ ልማት ስራ ተመራጭነቷን በማሳደግ ለዕድገቷ ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የኮሪደርና የመዳረሻ ልማቱ ለቱሪዝም እድገቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ያመለከቱት ደግሞ በቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት የከልነሪ አርት ከፍተኛ ኢንስትራክተር አቶ ጌትሽ ገደፋው ናቸው።
መንግስት የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያንሰራራ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።