ቀጥታ፡

ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነትና የልማት ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ ፊንላንድ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነትና የልማት ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ የፊንላንድ አምባሳደር ሲኒካ አንቲላ ገለጹ።

ኢትዮጵያና ፊንላንድ ለረጅም ዓመታት የዘለቀ ጠንካራ የዲፕሎማሲ እና የልማት አጋርነት እንዳላቸው የገለጹት አምባሳደሯ፣ በበርካታ መስኮች ውጤታማ ተግባራት ሲያከናወኑ መቆየታቸውንም ገልጸዋል። 

በሁለቱ አገራት መካከል በተለይም በትምህርት፣ በግብርና፣ በመሠረተ ልማት፣ በገጠር ልማትና በንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት ላይ ለበርካታ ዓመታት የዘለቀ ስኬታማ ትብብር መደረጉን በአብነት ጠቅሰዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ፊንላንድ በመሬት አስተዳደርና በዲጂታል የመሬት ምዝገባ ስራዎች ውጤታማ ትብብር ስታደርግ መቆየቷን ጠቁመዋል። 

ፊንላንድ አሁን ካለው የልማት ትብብር ባለፈ የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ወደ ጠንካራ የንግድና የኢኮኖሚ አጋርነት ለማሳደግ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ የዲጂታላይዜሽን ግብ የሚደነቅ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሯ፣ የፊንላንዱ ግዙፍ የቴክኖሎጂ ተቋም ኖኪያ ከሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ጋር እያከናወነ ያለው የጋራ ተግባር ለዚህ ጉዞ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በትምህርትና በቴክኖሎጂ ዘርፍ ያለውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

ፊንላንድ በሁሉም ረገድ የኢትዮጵያን የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ለመደገፍ ዝግጁ መሆኗንም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አዳዲስ የፈጠራ ስራዎችንና ስታርትአፖችን ለማበረታታት የያዘችው አቅጣጫ ተስፋ ሰጪ መሆኑን አምባሳደሯ ጠቁመዋል።

ፊንላንድ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንካራ የስታርትአፕ እንቅስቃሴ ካላቸው ሀገራት ተርታ እንደምትመደብ በማንሳት፣ በቀጣይ የሁለቱን ሀገራት ወጣቶችና የፈጠራ ባለቤቶች ለማገናኘት መታቀዱን ገልጸዋል።

ሀብትን በአግባቡ በመጠቀም ብክነትን መቀነስና የአካባቢ ጥበቃን ማረጋገጥ ላይ የተሰማሩ አዳዲስ ንግዶች በኢትዮጵያ ብቅ እያሉ መሆኑን አምባሳደሯ ገልጸው፤ ይህ ዘርፍ ለቀጣዩ የኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም