በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት በማደጉ በባለሙያ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ጨምሯል - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት በማደጉ በባለሙያ የሚወልዱ እናቶች ቁጥር ጨምሯል
ጎንደር፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦በማእከላዊ ጎንደር ዞን የጤና አገልግሎትን ጥራትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት በሰለጠኑ ባለሙያዎች የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር መጨመር መቻሉን የዞኑ ጤና መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ሃላፊ ሲስተር ምሳ ታረቀኝ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በተከናወኑ ተግባራት በወሊድ ወቅት በእናቶችና በጨቅላ ህጻናት ላይ የሚደርሰውን የሞት አደጋ መቀነስ ተችሏል፡፡
በዞኑ በሚገኙ 10 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች እንዲሁም በጤና ጣቢያዎችና ጤና ኬላዎች የወሊድ አገልግሎት እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚህም ባለፉት 9 ወራት በጤና ተቋማት የወለዱ እናቶች ቁጥር 40 ሺህ መድረሱን ጠቁመው ይህም ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10 ሺህ ብልጫ እንዳለው አስረድተዋል።
ለዚህም በጤና ተቋማት የነፍሰ ጡር እናቶች ማቆያ ቦታ በማዘጋጀት የተሟላ የምግብ፣ የመኝታ፣ የወለዱ እናቶች እንክብካቤና ሌሎች አገልግሎቶችን የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ በመፈጠሩ የመጣ ውጤት ነው ብለዋል።
ይህም በቤት ውስጥ በሚፈጸም ወሊድ የሚከሰተውን የህጻናት ሞት፣ በእናቶች ላይ የሚደርሰውን የፌስቱላ በሽታና ሌሎች ችግሮችን ማስወገድ መቻሉን አስረድተዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብም ለእናቶች ምግብ የሚሆን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥር እንዲጨምር የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል።
በዞኑ የወገራ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ባንቺአምላክ ገሰሰ፤ ሁለት ልጆቻቸውን በጤና ተቋማት በሰላም መገላገላቸውን ገልጸዋል፡፡
በወላድ እናቶች ማቆያው ነፍሰ ጡር እናት ከወሊድ በፊትም ሆነ በኋላ አካሏን የሚጠግን ገንፎና አጥሚትን ጨምሮ ሌሎች የተመጣጠኑ የምግብ ዓይነቶች በመቅረቡ ጤንነቷ ተጠብቆ እንድትወልድ አስችሏል ብለዋል።
በጤና ተቋማት የተዘጋጀው የእናቶች ማቆያ እናቶች ተገቢውን የህክምና ክትትል በማድረግ በሰላም እንዲገላገሉ እያስቻለ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ትርንጎ አቡሃይ ናቸው፡፡