ቀጥታ፡

ሚያዝያ 27 አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መጻፍ የተጀመረበት የትንሣኤ ጉዞ መሠረት ነው- የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ ሚያዝያ 27 የታሪክ ማኅደር ተገልጦ የሚነበብበት የትላንት ትዝታ ብቻ ሳይሆን፣ የአርበኞች አባቶችና እናቶች የድል መንፈስን እንደ ብዕር በመጠቀም አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መጻፍ የተጀመረበት የትንሣኤ ጉዞ መሠረት መሆኑን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ገለጸ።

ቀኑ ወጣቱ ትውልድ ሀገሩን በክብር ለመረከብ ላቡን የሚያፈስበትና የቁርጠኝነት ቃሉን የሚያድስበት የነፃነት ማስታወሻ መሆኑንም አመልክቷል።

ከ85 ዓመታት በፊት አባቶች በደምና በአጥንታቸው ሀገርን ጠብቆ የማቆየት ታሪካዊ ግዴታቸውን በድል እንደተወጡ ያስታወሰው አገልግሎቱ፤ ዛሬ የታሪኩ ምዕራፍ ተቀይሮ ተረኝነቱ የወጣቱ ትውልድ መሆኑን አሥፍሯል።

አባቶች በነፃነት ያቆዩልንን ሀገር በዕውቀት፣ በላብና በሥራ የመገንባት የዘመኑ አርበኝነት አደራ በትውልዱ ፊት መደቀኑም አስገንዝቧል።

አባቶች በጠመንጃ ሀገርን እንደጠበቁ ሁሉ፣ የአሁኑ ትውልድ በቴክኖሎጂ ሀገር የመገንባት፣ ድህነትን አሸንፎ ብልጽግናን የማረጋገጥና ለታላቅነት የመቆም ኃላፊነት እንዳለበት ተጠቁሟል።

ያለ አባቶች መስዋዕትነት ዛሬ የምትገነባው ሀገር እንደማትኖር ሁሉ፣ ያለ አሁኑ ትውልድ ግንባታም አባቶች የጠበቋት ሀገር ለዜጎቿ ትርጉም ያለው ሕይወት መስጠት እንደማትችል ተገልጿል።

ኢትዮጵያዊያን ከስንዴ ልመና ለመላቀቅ ማረሻቸውን ጨብጠው መነሳታቸው፣ 48 ቢሊዮን ችግኝ መተከሉ፣ የታላቁ የህዳሴ ግድብ እውን መሆንና ያረጁ ከተሞችን የመለወጥ ተግባራት የዚሁ የአደራ ቅብብል ውጤቶች መሆናቸውን አገልግሎቱ ገልጿል።

በተጨማሪም የከረሙ ስብራቶችን ለመጠገን የሚደረጉ ምክክሮች፣ የታዳሽ ኃይልና የአቪዬሽን ማዕከል ግንባታዎች ሀገርን በላብ የማሻገር አደራ መገለጫዎች መሆናቸው ተብራርቷል።

እያንዳንዱ ዜጋ በተሰማራበት የሥራ መስክ ሁሉ ለሀገሩ ጡብ የሚደረድር የዘመን አርበኛ መሆን እንደሚጠበቅበት አገልግሎቱ አሳስቧል።

ዛሬ የሚከናወኑ የልማት ሥራዎች፣ የሚታየው ጽኑ አንድነትና ዳር የሚደርሱ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ሀገርን ጠብቀው ላቆዩ አባቶች የሚሰጡ ትልቁ የክብር መግለጫዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ኢትዮጵያ በልጆቿ ላብ ታላቅ ትሆናለች ሲል አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም