ቀጥታ፡

በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች የ19 ቢሊዮን ብር ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ ቀርቧል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦በልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች አማካኝነት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 19 ቢሊዮን ብር ዋጋ ያለው ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ መቅረቡን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡  

ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የአምስት ቢሊዮን ብር ብልጫ የታየበት ሲሆን፣ የተካሄደው ሪፎርምና መንግሥት ያደረገው ድጋፍ ውጤት መሆኑም ተጠቁሟል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) "ኢትዮጵያ ታምርት ለሁለንተናዊ ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል የተዘጋጀውን አራተኛውን የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ኤክስፖ በከፈቱበት ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የኢንዱስትሪ ዘርፉ እያደገ መጥቷል።

የኢንዱስትሪ ዘርፉ ዕድገት የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሲጀመር ከነበረበት 4.7 በመቶ አሁን ላይ ወደ 10.7 በመቶ መድረሱን በወቅቱ ገልጸዋል። 

ባለፉት አራት ዓመታትም ከውጭ ይገባ የነበረን የ14.5 ቢሊዮን ዶላር ምርት በሀገር ውስጥ መተካት እንደተቻለም ነው የገለጹት።


 

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፍጹም ከተማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገቡ ኢንቨስተሮች ምርታቸውን 100 በመቶ ለውጭ ገበያ እንዲያቀርቡ የሚገደዱበት አሠራር ነበር። 

ሆኖም መንግሥት ባደረገው ሪፎርም አምራቾች ምርታቸውን 50 በመቶ ለውጭ፣ 50 በመቶ ደግሞ ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲያቀርቡ መፈቀዱን አስታውቀዋል።

ይህ አዲስ አቅጣጫ የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት ባለፈ፣ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በአገር ውስጥ ምርት ለመተካት (Import Substitution) ትልቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ተናግረዋል። 


 

በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት ብቻ ኮርፖሬሽኑ ከሚያስተዳድራቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች የ19 ቢሊዮን ብር ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ መቅረብ መቻሉን አመልክተዋል።

አሁን የተገኘው ውጤት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ የሆነ ልዩነት ያለው ምርት ለአገር ውስጥ እያቀረቡ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት በርካታ ፋብሪካዎች በግንባታና በማሽን ተከላ ሥራ ላይ የተሰማሩ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፤ እነዚህ ፋብሪካዎች በቅርቡ ወደ ምርት ሲገቡ የአገር ውስጥ ምርት አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያድግም አንስተዋል።


 

መንግሥት ያካሄደው ሪፎርምና ኮርፖሬሽኑ ባደረገው ልዩ ድጋፍና ማበረታቻ የተገኘው ውጤት በቀጣይ ዓመታት ይበልጥ እንዲጨምር በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። 

ኮርፖሬሽኑ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎችን በማስፋፋትና ለአምራቾች ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለመደገፍ የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም