የባህር ዳር ከተማን የቱሪስት መስህብነት ይበልጥ የሚያጎሉ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
የባህር ዳር ከተማን የቱሪስት መስህብነት ይበልጥ የሚያጎሉ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል
ባህር ዳር፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የባህር ዳር ከተማን የቱሪስት መስህብነት የሚያጎሉና የነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የችግኝ ተከላ ሥራዎችን ለማከናወን ዝግጅት መደረጉን የከተማዋ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
በመምሪያው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ አንዳርጋቸው ይርጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የችግኝ ዝግጅቱ በከተማዋ የተገነባውን የኮሪደር ልማትና የከተማዋን ተፈጥሯዊ ውበት ለማድመቅ መሰረት ያደረገ ነው።
በተያዘው በጋ የተዘጋጀውን ችግኝ በክረምቱ በከተማዋ በ562 ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ከዚህ ውስጥም ከ229 ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት ለአንድ ጀንበር የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር የተለየ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በችግኝ ዝግጅቱ እንደ ዱራንታና አሪዮካርፐስ ያሉ ማራኪ የውበት ዛፎች እንዲሁም የቡና፣ የአቮካዶ፣ የማንጎ፣ የፓፓያና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ይገኙበታል ብለዋል።
በተለይም የውበት ችግኞችን የኮሪደር ልማት በተሰራባቸው አካባቢዎች በመንገድ ዳርና በአረንጓዴ ስፍራዎች በመትከል ባህር ዳርን በቱሪስት መስህብነት የላቀች ለማድረግ እንደሚሰራ አስረድተዋል።
በችግኝ ማፍላት ስራውም በ25 የሽርክና ማህበር የተደራጁ 388 ወጣቶችን በማሳተፍ ዘላቂ የገቢ አቅማቸውን እንዲያሳድጉ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፈው ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከሉት ችግኞች ውስጥ 86 ነጥብ አምስት በመቶ የሚሆኑት መጽደቃቸውን በተካሄደ ቆጠራ ማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመው ይህም የከተማዋን የደን ሽፋን ከ26 በመቶ በላይ እንዲደርስ አስችሏል ብለዋል።
"የንጉሴ፣ ዘይድና ጓደኞቹ" ችግኞች ማፍላት ህብረት ስራ ማህበር ስራ አስኪያጅ ወጣት ንጉሴ ቻሌ እንደገለጸው፤ ካዘጋጁት ከ40 ሺህ በላይ ችግኞች ሽያጭ ከ300 ሺህ ብር በላይ ገቢ ለማግኘት እየሰሩ ነው።
የዛሬ 5 ዓመት ሦስት ሆነው በ20 ሺህ ብር ካፒታል በጀመሩት የችግኝ ማፍላት ስራ አሁን ላይ ካፒታላቸውን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ ችለዋል።
ከራሳቸው በተጨማሪም ስድስት ቋሚና እስከ 40 የሚደርሱ ጊዜያዊ ሰራተኞችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል።
"የደረጀ ሰራ ወርቅና ጓደኞቻቸው" ችግኝ ማፍላት ሽርክና ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛቸው ሰለሞን በበኩላቸው፤ ከ10 ዓመት በፊት ከጡረታ ጊዜያቸው በኋላ ወጣቶችን በማስተባበር ወደ ስራ እንደገቡ አስታውሰዋል፡፡
በተያዘው በጋም 120ሺህ የተለያዩ ችግኞችን ማፍላታቸውን ጠቁመው ከችግኝ ሽያጩ ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን አረጋግጠዋል።