የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ መታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ መታሰቢያ ሐውልት ተመረቀ
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 27/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በስድስት ኪሎ አካባቢ የተገነባውን የአርቲስት ጥላሁን ገሠሠን መታሰቢያ ሐውልት መርቀዋል።
በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣የጥበብ ቤተሰቦች፣አንጋፋና ወጣት አርቲስቶች እንዲሁም በርካታ አድናቂዎቹ ተገኝተዋል።
ይህ የመታሰቢያ ሐውልት አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የነበረውን ጉልህ ሚና እና ለበርካታ አስርት ዓመታት ያበረከተውን የማይረሳ አስተዋጽኦ የሚዘክር ነው።
አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ "የኢትዮጵያ ሙዚቃ ንጉሥ" በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ ከ400 በላይ የሚሆኑ ሥራዎቹ የሀገሪቱን ባህል፣ ፍቅር እና ማህበራዊ እሴቶች የጠበቁ ናቸው።
አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ የኢትዮጵያን ሙዚቃ ከባህላዊ ወደ ዘመናዊ በማሸጋገር ረገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው።
በተለይም ድምፁን እንደ መሣሪያ የመጠቀም ልዩ ተሰጥኦው ለብዙ ትውልድ ድምፃውያን እንደ ትምህርት ቤት ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል።
በስድስት ኪሎ የቆመው ሐውልት፣ አርቲስቱ ለጥበብና ለሀገሩ የከፈለውን መስዋዕትነት ለትውልድ የሚያስተላልፍ ከመሆኑም በላይ፣ ለኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች የሚሰጠውን ክብር የሚያሳይ ነው።
አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት እንደተሰጠው ይታወቃል።
ዩኒቨርሲቲው የክብር ዶክትሬት የሰጠው አርቲስቱ ለኢትዮጵያ ሙዚቃ እድገት ላበረከተው የላቀ አስተዋጽኦ እና በኪነ-ጥበብ አማካኝነት ሀገሩን ለማገልገል ላሳየው ቁርጠኝነት እውቅና ለመስጠት ነው።
አርቲስት ጥላሁን ገሠሠ መስከረም 17 ቀን 1933 ዓ.ም ተወልዶ፣ ሚያዝያ 11 ቀን 2001 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ይታወሳል።