የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በሥራ ዕድልና በቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ አድርጎናል - ኢዜአ አማርኛ
የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት በሥራ ዕድልና በቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ አድርጎናል
ሐረር፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦በሐረሪ ክልል የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት፤ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም ባለፈ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ክህሎታቸውን በማሳደግ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው የእድሉ ተጠቃሚዎች ገለጹ።
የሐረሪ ክልል በታሪኩና በቱሪስት መስህብነቱ ቢታወቅም፣ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የክልሉን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በኢንዱስትሪ ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።
በተለይም መንግስት የኢንዱስትሪዎችን ምርታማነት ለማሳደግና የውጭ ምንዛሬን ለማዳን የጀመረው "ኢትዮጵያ ታምርት" ንቅናቄ በክልሉ ውጤት ማምጣት ጀምሯል።
ክልሉ ለኢንቨስትመንት አመቺ የሆኑ የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎችን በማጠናከር፣ አዳዲስ ፋብሪካዎች ወደ ሥራ እንዲገቡና ነባሮቹ ደግሞ በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ እያደረገ ያለው ጥረት ለዜጎች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ፣ የኢንዱስትሪ ባህልና የቴክኖሎጂ ዕውቀት በአካባቢው እንዲሰርጽ እያደረገ ይገኛል።
ወጣት ፈርሃን ተውፊቅ የሐረር ከተማ ተወላጅ ሲሆን በከተማው ኢንዱስትሪ ዞን በሚገኘው ማስ ኢንጅነሪንግ ኢንተርፕራይዝ በተለያዩ የሙያ ዘርፍ እርሱና ሌሎች ጓደኞቹ የስራ እድል እንደተፈጠረላቸው ተናግሯል።
በክልሉ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት የተሻለ የቴክኖሎጂ ክህሎት እንዲያገኙ ከማስቻሉ ባለፈ ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በኢንተርፕራይዙ በማምረት የውጭ ምንዛሬን የማስቀረት ተግባር እያከናወኑ መሆኑን አስረድቷል።
በከተማው በብረታብረት ዘርፍ ወደ ስራ በመግባት ከኢንዳስትሪው ባገኙት የስራ እድል ተጠቃሚ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ነስረዲን አህመድ ናቸው።
በተለይም የኢንዱስትሪዎች መስፋፋት ለከተማዋ የኮሪደር ልማት የሚውሉ የፖል ብረት ምርቶች በስፋት እንዲቀርቡና ከተማዋን እንዲያስውቡ ማድረጉን አቶ ነስረዲን ገልጸዋል።
በዱቄት ፋብሪካ የስራ ዕድል ተጠቃሚ በመሆኗ እራሷንና ቤተሰቧን እያገዘች መሆኑን የገለጸችው ደግሞ ወጣት ኤደን ፍሰሃ ናት።
በሐረር የኢንዱስትሪዎች መነቃቃት ለስራ ፈላጊውም ጭምር አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ተናግራለች።
ከዚህ ባለፈም ልምድ፣ ተሞክሮና የተሻሻሉ አሰራሮችን እየቀሰሙ እንደሚገኙ የገለጸችው ወጣት ኤደን፣ በዚህም ለፋብሪካ ባለቤቶች ምስጋና አቅርባለች።
ፋብሪካው 120 ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል ፈጥሯል ያሉት ደግሞ በከተማው ኢንዱስትሪ ዞን የሚገኘው የቀነኒ ዱቄት ፋብሪካ ስራ አስኪያጅ አቶ ተስፋ አስፋው ናቸው።
ፋብሪካው በአሁኑ ወቅት ከውጪ ይገባ የነበረውን የስንዴ ዱቄት በአገር ውስጥ በማምረት እና ለአካባቢው በማከፋፈል ላይ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም የፓስታ፣ መኮሮኒን እና ሌሎች ምርቶችን ለማምረት የዝግጅት ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የሐረሪ ክልል ኢንተርፕራይዞች ልማትና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ አቶ ኡስማኢል ዩስፍ በበኩላቸው፤ በክልሉ አዳዲስና ነባር መካከለኛና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችን ወደ ስራ በማስገባት ተኪ ምርቶችን በስፋት የማምረት ተግባር መጠናከሩን ተናግረዋል።
በተለይም የክልሉን ኢኮኖሚ ይበልጥ የሚያጎለብቱና የስራ እድልን የሚያስፋፉ ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ግንባታቸው ተጠናቆ ማሽነሪዎችን የማስገባት ስራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።