በወሰድነው ካርድ ሀገር የሚመራ ፓርቲ ለመምረጥ የድምፅ መስጫውን እለት እየተጠባበቅን እንገኛለን - ኢዜአ አማርኛ
በወሰድነው ካርድ ሀገር የሚመራ ፓርቲ ለመምረጥ የድምፅ መስጫውን እለት እየተጠባበቅን እንገኛለን
አርባምንጭ ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በጠቅላላ ምርጫው ለወሰድነው ካርድ ዋጋ ለመስጠት የድምፅ መስጫውን እለት እየተጠባበቅን እንገኛለን ሲሉ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ።
ተማሪዎቹ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በልዩ ሁኔታ እንዲመዘገቡ በተመቻቸላቸው ዕድል መሠረት የመራጭነት ካርዳቸውን መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ ለምርጫ የተዘጋጁበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን ያነሱት ተማሪዎቹ ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፃቸውን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው ተገኝቶ የኢዜአ ሪፖርተር ካነጋገራቸው ተማሪዎች መካከል ተማሪ ሰለሞን ሳሙኤል፣ ተማሪ ደህናሰው ዋስይሁን እና ተማሪ ኢዮብ ፍቅሬ በምርጫው የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ለሀገር ልማትና ዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ በምርጫ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ተማሪዎቹ ለወሰዱት ካርድ ዋጋ ለመስጠት የድምፅ መስጫውን እለት እየተጠባበቅን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል።
የምርጫ ጉዳይ የጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ እና የዴሞክራሲ ስርአት እድገት ልምምድ በመሆኑ በእንዲህ አይነት ታሪካዊ አጋጣሚዎች ጠንካራ ተሳትፎ ማድረግ ይገባል ሲሉም አንስተዋል።
የምርጫው ሂደት ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ በተለይም የወጣቶች እገዛ፣ ትብብርና ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ሀገራዊ ሃላፊነታችንን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ አረጋግጠዋል።
የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማንፌስቷቸውንና የምርጫ ምልክቶቻቸውን በማስተዋወቅ የምረጡኝ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ መሆናቸው ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መርሃ ግብር መሰረትም የድምጽ መስጫ እለት ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይሆናል።