በምዕራብ ሸዋ ዞን የወባ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ሸዋ ዞን የወባ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በቅንጅት እየተሰራ ነው
አምቦ ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን የወባ በሽታ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ የተቀናጁ የጥንቃቄ ሥራዎች በትኩረት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ጤና ጽሕፈት ቤት ገለጸ።
በጽህፈት ቤቱ የወባ መከላከያ እና መቆጣጠሪያ ባለሙያ ዶክተር አባተ አርጋው ለኢዜአ እንደገለጹት እየጣለ ያለውን የበልግ ዝናብ ተከትሎ የወባ ትንኝ ስርጭት እየጨመረ መጥቷል።
በተለይም በዞኑ እንደ ባኮ ቲቤ፣ ኢሉ ጋላን፣ ዳኖ እና ኖኖ ወረዳዎች በዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመሆኑም የበሽታውን ስርጭት የመከላከልና መቆጣጠር ሥራዎች ላይ በዞኑ ሁሉም መዋቅሮች በቅንጅትና በርብርብ እየተሰራ መሆኑን ነው ያመላከቱት።
የወባ በሽታን የምታስተላልፈው ትንኝ ምቹ መራቢያ የሆኑ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን ማፋሰስና የማዳፈን፣ የአካባቢ ፅዳትን ማጠናከርና፣ አጎበርን በተገቢው መጠቀም እንዲቻል የማስገንዘብ ስራ በየደረጃው እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የአካባቢ ቁጥጥር ስራን በማጠናከር፣ ኬሚካል የተነከረ የአልጋ አጎበር ስርጭት በመጠቀምና በበሽታው የታመሙትን ደግሞ በአቅራቢያው በሚገኙ ጤና ተቋማት የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ትኩረት ከተሰጣቸው ተግባራት መሆናቸውን አውስተዋል።
በዚህ ረገድ በዞኑ ከ259 ሺህ በላይ የአልጋ አጎበር ለነዋሪው መሰራጨቱንና በአግባቡ እንዲጠቀሙ ትምህርት መሰጠቱን ጠቁመዋል።
እንዲሁም በወባ በሽታ ተይዘው የመጡ ሰዎች በየደረጃው በሚገኙ ጤና ተቋማት ታክመው መዳናቸውን አስረድተዋል።
የበሽታውን ስርጭት አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻልም 245 ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች ስለ በሽታው የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መሰጠቱን አስታውቀዋል።
ወባን ለመከላከል እየተደረገ ባለው ጥረት በዞኑ የወባ በሽታ ስርጭት መጠን ከዓምናው መሻሻል ማሳየቱንም ዶክተር አባተ አብራርተዋል።
የዞኑ ነዋሪዎች በበኩላቸው የበሽታው ስርጭት እንዳይስፋፋ በጤና ልማት ቡድን አማካኝነት አካባቢያቸውን የማፅዳት ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።