በምስራቅ ጎጃም ዞን አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ተደርጓል
ደብረ ማርቆስ ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በምስራቅ ጎጃም ዞን አሲዳማ አፈርን በኖራ በማከም ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ጥላሁን ንጋቱ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በመጪው መኸር ምርትና ምርታማነትን በሁሉም አማራጭ በማሳደግ በምግብ ራስን ለመቻል ርብርብ እየተደረገ ነው።
በዚህም ከ46 ሺህ ሄክታር በላይ በአሲድ የተጠቃ መሬትን በኖራ በማከም ቀድሞ ወደ ነበረበት ምርታማነት ለመመለስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኖራ አቅርቦት ዙሪያ ከአቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር በፍጥነት ለአርሶ አደሩ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን እስካሁን ከ3ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱን ተናግረዋል።
በቀጣይ ወራትም አስፈላጊውን መጠን ኖራ በማቅረብ አሲዳማ የሆነውን አፈር የማከሙ ተግባር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በመኸር ምርቱ የታቀደውን የምርት ጭማሪ ለማስመዝገብም መሬትን በኖራ ከማከም ባሻገር አዳዲስ አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ላይ በማተኮር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዞኑ የማቻከል ወረዳ የቅዳማን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ባየልኝ ሙላት እንደገለጹት በአሲድ የተጠቃውን አንድ ሄክታር ማሳቸውን በኖራ በማከም ዘር እየዘሩ ነው።
በኖራ አክመው ከሚዘሩት ሰብል ከአምስት ኩንታል በላይ የምርት ጭማሪ እንዳገኙ ጠቁመው ያገኙትን ጥቅም ለማሳደግም ዘንድሮ ከ30 ኩንታል በላይ ኖራ ማሳቸው ላይ መበተናቸውን ተናግረዋል።
በአነደድ ወረዳ የጉዳለማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጊዜአለው አግደውም ማሳቸውን በኖራ በማከም ለምነቱ እንዲመለስ እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይም ከግማሽ ሄክታር በላይ ማሳቸው ላይ ኖራ በመበተን ደጋግመው ማረሳቸውን ጠቁመው በቀጣይም ከዘሩ ጋር ቀላቅለው በመዝራት ምርታማነታቸውን ለማሳደግ እንደሚሰሩም አመልክተዋል።
በመጪው የመኸር ምርት ከ660 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በተለያዩ ሰብሎች በማልማት ከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱ ተመልክቷል።