በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገርና ለሕዝብ ይበጃል የምንለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገርና ለሕዝብ ይበጃል የምንለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅተናል
ጎዴ፣ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሀገርና ለሕዝብ ይበጃል የሚሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውን የጎዴ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
በየአምስት ዓመቱ የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ መብታቸው መገለጫ መሆኑን የገለጹት የከተማዋ ነዋሪዎች፤ የምርጫ ካርዳቸውን በመውሰድ የድምፅ መስጫውን ዕለት እየተጠባበቁ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
አቶ አህመድ አስከር አበዲራህማን ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በመውሰድ በድምፅ መስጫ ዕለት የኢትዮጵያን ዕድገትና ልማት ያፋጥናል ብዬ የማምነውን ፓርቲ በድምጽ ለመምረጥ ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።
በአንድ አገር የዴሞክራሲ መጎልበት የዜጎች ንቁ ተሳትፎ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የገለጹት አስተያየት ሰጪው፤ የድምፅ መሰጫ እለቱን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
አቶ ነዲር ቃሲም አብዲ በበኩላቸው፤ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን ገልጸው፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ማኒፌስቶዋቸውን እና የምርጫ ምልክቶቻቸውን ለሕዝብ በማስተዋወቅ እያደረጉት ያለው የቅስቀሳ እንቅስቃሴ የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
በምርጫው የድምፅ መስጫ ዕለት በንቃት በመሳተፍ፣ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንደሚያረጋግጡም ገልጸዋል።
ዜጎች የመምረጥ መብታቸውን በአግባቡ መጠቀማቸው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ቁልፍ ሚና እንዳለውም አስገንዝበዋል።
በተመሳሳይ ወጣት ራቢዕ መሀመድ በበኩሉ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምፁን ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል።
በዚህም ማንኛውም የምርጫ ካርድ የወሰደ ዜጋ፣ በድምፅ መስጫው ዕለት መሳተፍ እንዳለበት ተናግሯል።
ንምኦ ሶአኔ በበኩሏ፤ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የመራጭነት ካርድ መውሰዷን ገልጻ፤ በድምፅ መስጫው ዕለት ለሀገርና ለህዝብ ይበጃል ብላ የምታምንበትን ፓርቲ ለመምረጥ በመጠባበቅ ላይ መሆኗን ተናግራለች።