በክልሉ የቡና ኢንሼቲቭ ግቦችን ለማሳካት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን የማስፋት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቡና ኢንሼቲቭ ግቦችን ለማሳካት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን የማስፋት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ ነው
አዳማ ፣ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የቡና ኢንሼቲቭ ግቦችን ለማሳካት፤ የተሻለ ምርት የሚሰጡ ዝርያዎችን የማስፋት ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሙሐመድሳኒ አሚን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የቡና ምርታማነትን ለመጨመር የተሻለ ምርት የሚሰጡ ችግኞች ለአርሶ አደሩ በስፋት ተደራሽ እየሆኑ ይገኛሉ።
የቡና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ አንዱ የትኩረት አቅጣጫችን በምርምር የተሻሻሉ የቡና ዝሪያዎችን ለአርሶአደሩ በስፋት ተደራሽ ማድረግ ነው ብለዋል።
በክልሉ ለዘንድሮው የቡና ልማት በቂ የቡና ችግኞች ተዘጋጅተዋል ያሉት የቢሮው ምክትል ሃላፊ፤ በአሁኑ ወቅት የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የችግኞቹ ተከላ እየተከናወነ ይገኛል ነው ያሉት።
በዘንድሮው የቡና ችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ከ200 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ለመሸፈን ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የችግኝ ተከላው በሳይንሳዊ ዘዴ እንዲመራ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፤ ለዘርፉ ባለሙያዎችና ለአርሶ አደሮች አስፈላጊው ስልጠና መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
ምርት የማይሰጡና ያረጁ የቡና ዛፎችን የመንቀልና የተሻለ ምርት በሚሰጡ በአዲስ ዝሪያ የመተካት ስራ ከማከናወን ባለፈ የጉንደላ ስራም በስፋት መከናወኑን ተናግረዋል።
በእስካሁኑ ሂደት ያረጀና ተገቢውን ምርት የማይሰጥ ቡና በመንቀል በ66ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የተሻለ ምርት የሚሰጡ የቡና ችግኞች መተከላቸውን ተናግረዋል።
በተመሳሳይ ባረጀ የቡና ጉንደላ ስራ ከ120ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ያለውን ተክል መሸፈን መቻሉንም ጨምረው ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት የቡና ችግኞችን በስፋት ለመትከል የሚያስችል አስተማማኝ የዝናብ ሁኔታ መኖሩን የገለጹት አቶ ሙሐመድሳኒ፤ አርሶ አደሩ በሙሉ አቅሙ ተከላውን በማከናወን ጊዜውን በአግባቡ እንዲጠቀም ተገቢውን ድጋፍና ክትትል እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ በዘንድሮው ዓመት 16 ሚሊዮን ኩንታል የቡና ምርት መሰብሰቡን የገለፁት አቶ ሙሐመሳኒ ባለፉት ዘጠኝ ወራት 251 ሺህ ቶን ቡና ለማዕከላዊ ገበያ መቅረቡንም ጨምረው ተናግረዋል።