ቀጥታ፡

አርበኝነት ማለት ለሀገር ያለ ዋጋ የሚከፈል ከራስ ወዳድነት የነጻ መሥዋዕትነት ነው

አዲስ አበባ፣ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ)፦አርበኝነት ማለት ለሀገር ያለ ዋጋ የሚከፈል ከራስ ወዳድነት የነጻ መሥዋዕትነት ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ85ኛው የጀግኖች አርበኞች በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

እንኳን ለ85ኛው የጀግኖች አርበኞች በዓል አደረሳችሁ

ሚያዝያ 27 ቀን ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች የፋሽስትን ወረራ የቀለበሱበትና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ሙሉ በሙሉ ያስከበሩበት በዓል ነው።

አርበኝነት ማለት ለሀገር ያለ ዋጋ የሚከፈል ከራስ ወዳድነት የነጻ መሥዋዕትነት ነው። ዓላማውም ሀገርንና ሕዝብን ብቻ ማዕከል ያደረገ ነው። ለግል ወይም ለቡድን በተለየ የሚገኝ ነገር የለውም። ለሀገር ከሚገኘው ነጻነት፣ ሉዓላዊነት እና ክብር ከሚደርስ የዜጋ ድርሻ በቀር።

እናትና አባት አርበኞች ከፋሺስት ጋር የተዋጉት ለሀገር እና ለወገን ብለው ነው። በግል ጥቅም ለማግኘትማ ከአርበኝነት ይልቅ ባንዳነት አቋራጭ ነበር። ግን አላደረጉትም።

የአርበኝነት ትግሉ ከሦስት ጠላቶች ጋር የተደረገ ነበር። ከራስ ፍላጎት፣ ከባንዳና ከወራሪ ፋሺስት ጋር። አርበኝነት የራስን ጥቅም ለሀገር ጥቅም ሲባል መተው ነው። አርበኝነት የግል ክብርን፣ የግል ሥልጣንን እና የግል ጥቅምን መሠዋት ነው። ይሄንን ለመቀበል ከጠላት በፊት ራስን ማሸነፍ ይጠይቃል።

ባንዳዎች ማለት ራሳቸውን ማሸነፍ ያቃታቸው ናቸው። የግል ጥቅምንና ክብርን ማሸነፍ ሲያቅታቸው የሀገራቸውን ክብርና ጥቅም ይሸጣሉ። ባንዳነት ማለት ሀገርን ለራስ ጥቅም በመሸጥ የሚከናነቡት የውርደት ካባ ነው። አርበኞች ከባንዳዎች ጋር ታግለዋል። ባንዳዎች በአንድ በኩል ሀገራችሁን ሽጣችሁ እንደኛ በግል ተጠቀሙ ይሏቸዋል። በሌላ በኩል መንገድ እየመሩ ወራሪውን ያመጡባቸዋል። ያም አልሆን ሲላቸው ሕዝቡን በሐሰተኛ ወሬ ልቡን ይሰልቡባቸዋል።

ዛሬም ሦስቱም ጠላቶች አሉ። መልክና ስም ብቻ ቀይረዋል። በሌላም በኩል ዛሬም በየመስኩ የተሠማሩ ኢትዮጵያውያን አርበኞች አሉ።

የኢትዮጵያ ብልጽግና እንዲሳካ ብሔራዊ አርበኞችን ይፈልጋል። የራስ ፍላጎትን፣ ባንዳነትን እና ወራሪን እምቢ የሚል አርበኝነት።

የኢንዱስትሪ አርበኞች፣ የግብርና አርበኞች፣ የጸጥታ አርበኞች፣ የፖለቲካ አርበኞች፣ የንግድ አርበኞች፣ የዲፕሎማሲ አርበኞች፣ የመንግሥት አገልጋይ አርበኞች፣ የሕክምና አርበኞች፣ የትምህርት አርበኞች፣ ወዘተ. ያስፈልጉናል።

ይሄንን በዓል የምናከብረው የየራሳችንን የአርበኝነት ደረጃ በመገምገም ነው። ለኢትዮጵያ ምን ያህል አርበኞች ነን?

ዛሬም የግል ፍላጎት የሚያሸንፋቸው ደካሞች አሉ። ሀገርን አፍርሰው የግል ቤት መሥራት የሚመኙ። ትልቁን መርከብ አፍርሰው ትንንሽ ታንኳዎችን ለመሸጥ የሚመኙ። ለቅንጥብጣቢ ነገር ውርደትን ለመሸከም የማይሰቀቁ።

ዛሬም ወራሪዎች አሉ። በአካል ሀገርን ለመውረር ካሰፈሰፉት በተጨማሪ ድህነት፣ ኋላቀርነትና ሌብነት የሚባሉ እንደ ሰርዶ ሀገርን ወርረው ሽባ የሚያደርጉ ጠላቶች አሉ። ሀገርን ለባዳ ከሚሸጡት ባንዳዎች እኩል፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የሚሸጡ ባንዳዎች አሉ። አገልግሎትንና የሕዝብን ሀብት የሚሸቅጡ ባንዳዎች አሉ።

ብሔራዊ አርበኝነት ማለት እነዚህን ሦስት ጠላቶች ታግሎ ማሸነፍ ማለት ነው። ዛሬ የምናየውን የኢትዮጵያ ለውጥና ዕድገት ማስመዝገብ የተቻለው ብሔራዊ አርበኞች በየአካባቢው በመኖራቸው ነው። ብሔራዊ አርበኞች ሦስቱን ጠላቶች እያሸነፉ ቢሆንም ገና ሙሉ በሙሉ ድልን አልተቀዳጁም።

ድሉ እንደ ሚያዝያ 27 የሚታወጀው ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ስትሆን ነው። ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ ከሚገኙ ኃያል ሀገሮች አንዷ ስትሆን ነው።

ይሄንን ድል እውን ለማድረግ ኢትዮጵያን የሚወዱ የኢትዮጵያ አርበኞች ሁሉ እንዲነሡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ሚያዝያ 27፣ 2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም