የዋንጫ ተፎካካሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የዋንጫ ተፎካካሪው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 27/2018 (ኢዜአ):- የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዛሬ ይጠናቀቃል።
ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ቦሌ ክፍለ ከተማ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ቦሌ ክፍለ ከተማ በ40 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ60 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ባለፉት ሶስት የሊጉ ጨዋታዎች ያሸነፈው ቦሌ ክፍለ ከተማ በድል ጉዞው ለመቀጠል ይፋለማል።
ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ካሸነፈ ከሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በነጥብ እኩል ይሆናል።
ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ አበባ ከተማ ከአዳማ ከተማ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይጫወታሉ።
አዲስ አበባ ከተማ በ11 ነጥብ 13ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። አዳማ ከተማ በ21 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።
በወራጅ ቀጠና የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማ ከተሸነፈ ከሊጉ ሊወርድ የሚችልበት እድል አለ።
ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ከድል የራቀው አዳማ ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይጫወታል።