የ30ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች መርሐ ግብር - ኢዜአ አማርኛ
የ30ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች መርሐ ግብር
አዲስ አበባ፤ ሚያዚያ 27/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ምድረ ገነት ሽሬ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ምድረ ገነት ሽሬ በ30 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ42 ነጥብ ስድስተኛ ደረጃን ይዟል።
ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚታገለው ምድረ ገነት ሽሬ፣ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ዛሬ የመጀመሪያ ድሉን ለማስመዝገብና ወሳኝ ሦስት ነጥብ ለመሰብሰብ ወደ ሜዳ ይገባል::
ካለፉት ሁለት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ማሸነፍ ወደ ድል መንገድ ይመልሰዋል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
የ2016 ዓ.ም የሊጉ ሻምፒዮን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ35 ነጥብ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ የ16 ጊዜ የሊጉ የዋንጫ ባለቤት ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በአንድ ነጥብ ብልጫ (36 ነጥብ) 11ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ላይ ሶስት ነጥብ ማግኘት አልቻለም። ተጋጣሚው ቅዱስ ጊዮርጊስም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ላይ ድል አልቀናውም።
ሁለቱም ክለቦች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማሉ።
ድሬዳዋ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።
ካለፉት ሶስት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ያገኘው ድሬዳዋ ከተማ በ33 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ኢትዮጵያ ቡና በ41 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡናማዎቹ በ29ኛ ሳምንት በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የ4 ለ 2 ሽንፈት አስተናግደዋል።
ጨዋታው ድሬዳዋ ከተማ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት፣ ኢትዮጵያ ቡና ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ መቀሌ 70 እንደርታ ከአርባምንጭ ከተማ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቀሌ 70 እንደርታ በ30 ነጥብ 19ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል። አርባምንጭ ከተማ በ25 ነጥብ የመጨረሻውን 20ኛ ደረጃን ይዟል።
በ29ኛ ሳምንት ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር አንድ አቻ የተለያየው መቀሌ 70 እንደርታ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከወራጅ ቀጠና ለመውጣት በሚያደርገው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
ባለፉት አራት የሊግ ጨዋታዎች ከድል የራቀው አርባምንጭ ከተማ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም የዛሬውን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
በወራጅ ቀጠና የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች የሚያደርጉት ጨዋታ ጠንካራ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል።