ቀጥታ፡

የሳይበር ደህንነት የቁልፍ መሠረተ ልማቶች ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2018(ኢዜአ)፦ የሳይበር ደህንነት የቁልፍ መሠረተ ልማቶች ረቂቅ አዋጅ የኢትዮጵያን የዲጂታል ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ዲማ ኖጎ (ዶ/ር) ገለጹ።

ቋሚ ኮሚቴው በቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደህንነት ረቂቅ አዋጅ ላይ የአስረጅ መድረክ አካሂዷል።


 

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሐሚድ በዚሁ ወቅት፤ ቁልፍ መሠረተ ልማቶች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን የሚያፋጥኑ ወሳኝ የሀገር ሀብቶች ናቸው ብለዋል።

ዘርፎቹ ከሌሎች መስኮች ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተያያዥነት ያላቸው በመሆናቸው፤ ጥቃት ቢፈጸምባቸው በብሔራዊ ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ተናግረዋል።


 

ይህም በሀገራዊ ደህንነትና በዜጎች የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል አስረድተዋል።

የሳይበር ደህንነት የቁልፍ መሠረተ ልማቶች ረቂቅ አዋጅም የሳይበር ተጋላጭነትና ሥጋትን ለመከላከል እንደሚረዳ አመልክተዋል።

የረቂቅ አዋጁ ዋና መነሻ የሳይበር ደህንነት ጥቃት አዝማሚያዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።

ረቂቅ አዋጁ ከጸደቀ የግሉን ዘርፍ ጭምር በማሳተፍ መንግስት በዘርፉ ሲያከናውናቸው የነበሩ ተግባራትን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚረዳ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ረቂቅ አዋጁ የሀገሪቱን ሕገ-መንግስት እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለምአቀፍ ሕጎች ጋር እንዲጣጣም ተደርጎ መዘጋጀቱ ተመላክቷል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር ዴኤታ ጂቱ ኢዶሳ (ዶ/ር)፤ ረቂቅ አዋጁ የተቋማትን ደህንነት በመጠበቅ "ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030"ን እውን ለማድረግ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።


 

በፍትሕ ሚኒስቴር ዓቃቤ ሕግ ደሳለ ጫኔ በበኩላቸው፤ ረቂቁ ከሚኒስቴሩ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች ተደርገውበት ወደ ቋሚ ኮሚቴው መመራቱን አውስተዋል።


 

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር)፤ ረቂቅ አዋጁ በተለዋዋጭ ዓለም የተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።


 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አምባሳደር ዲማ ኖጎ (ዶ/ር)፤ ረቂቅ አዋጁ ሀገራዊ የዲጂታል ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በቁልፍ መሣሪያነት እንደሚያገለግል አስገንዝበዋል።

የሳይበር ደህንነት የቁልፍ መሠረተ ልማቶች ረቂቅ አዋጅ ዝግጅት ሂደትም በፍጥነት ተጠናቆ ወደ ሥራ መግባት እንዳለበት አሳስበዋል።

ረቂቅ አዋጁ በቀጣይ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተጨማሪ ውይይት እንደሚደረግበት ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም