ቀጥታ፡

በአፋር ክልል የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ ነው

ሰመራ፣ሚያዚያ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ።

የአፋር ክልል ከጤና ሚኒስቴር የተበረከቱለትን ሰባት መደበኛ አምቡላንሶች እና አንድ ተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግሎት መስጫ ተሽከርካሪ ለተለያዩ ዞኖች አስረክቧል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ፤ በዚሁ መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ተሽከርካሪዎችን ለሚመለከታቸው የስራ ሃላፊዎች አስረክበዋል።


 

ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክትም፤ በክልሉ የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን የማስፋት ስራ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል። 

በተለይም ደግሞ ለአርብቶ አደር አካባቢዎች የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማሳደግ የተቀናጀ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት ለተለያዩ ዞኖች የተላለፉት አምቡላንሶችም በተለይም የአርብቶ አደሩን ማህበረሰብ የጤና አገልግሎት ለማሻሻል፤ የእናቶችና የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ እንዲሁም አፋጣኝ የህክምና እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ጉልህ ድርሻ እንዳላቸው አንስተዋል።

በመሆኑም የዜጎችን በተለይም ደግሞ የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለመጠበቅ በመንግስት የሚደረገው ጥረት እንዳለ ሆኖ የአጋር አካላት እገዛና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።


 

የክልሉ ጤና ቢሮ ኀላፊ ያሲን ሀቢብ፤ በክልሉ የዜጎችን የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ለማስፋት ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

በዛሬው እለት የተረከቧቸው አምቡላንሶችም የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆናቸውን አንስተው በሁሉም አካባቢዎች ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም