ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን አጠናክሯል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መሪነቱን አጠናክሯል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የ24ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድሬዳዋ ከተማን 4 ለ 0 ረቷል።
በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ረድኤት አስረሳኸኝ ሁለት ግቦችን ስታስቆጥር ቅድስት ዘለቀ እና ሰላማዊት ጎሳዬ ቀሪዎቹን ጎሎች ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ እመቤት አዲሱ የጨዋታው ኮከብ ሆና ተመርጣለች።
በሊጉ 20ኛ ድሉን ያስመዘገበው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ63 ነጥብ መሪነቱን አጠናክሯል። ከተከታዩ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የነጥብ ልዩነቱን ወደ ሶስት ከፍ አድርጓል።
በአንጻሩ በውድድር ዓመቱ ለ14ኛ ጊዜ የተሸነፈው ድሬዳዋ ከተማ በ24 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ቡድኑ ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንኳ ረድኤት አስረሳኸኝ በሊጉ ያስቆጠረቻቸውን ጎሎች ብዛት ወደ 20 ከፍ በማድረግ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን የምትመራውን የኢትዮ ኤሌክትሪኳ አጥቂ ዳግማዊት ሰሎሞን (23 ጎሎች) ትከተላለች።
ዛሬ በተደረገ ሌላኛው ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ ይርጋጨፌ ቡናን 2 ለ 0 አሸንፏል።