ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ዕውቅና አስገኝቷል 

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 26/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ የህብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓት ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማስገኘቱን የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የማርበርግ ቫይረስ ክትባት ክሊኒካዊ ሙከራ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ በሂደቱ በቁርጠኝነት ለሰሩ አካላት የዕውቅና መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

በዚህ ወቅት የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የጤና ሥርዓት ምርምር፣ ቁጥጥርና የአደጋ ጊዜ ምላሽ አሰጣጥ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው ብለዋል።


 

የመጀመሪያ ደረጃ ጤና ክብካቤ ተደራሽነት መስፋፋቱን ተከትሎም ባለፉት ስምንት ዓመታት የግል ጤና ተቋማትን ከ7 ሺህ ወደ 32 ሺህ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።

የጤና ተቋማት አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራትም የሪፈራል ሥርዓትን ከማሻሻል ባሻገር ለዘርፉ የምርምር ውጤታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

በቅርቡ በአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የተመረቀው የጤና ምርምር ላቦራቶሪ የመሰሉ የምርምር አቅምን የሚያሳድጉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።


 

የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ማቹሪቲ ደረጃ ሶስት መድረሱም ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት መኖሩን እንደሚያመላክት አንስተዋል።

የማርበርግ ክትባት ክሊኒካዊ ሙከራ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅም ለኢትዮጵያ የሳይንስና የሕብረተሰብ ጤና ዘርፍ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀጣይም ኢትዮጵያን ሳይንሳዊ የጤና ምርምር በማላቅ ለዓለም አቀፍ ሳይንሳዊ የምርምር ውጤታማነት በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።


 

የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ፤ ለማርበርግ ቫይረስ  አፋጣኝ ህክምና ከመስጠት ባለፈ ለክትባቱ የክሊኒካል ሙከራ መደረጉን ተናግረዋል።

የክሊኒካል ሙከራው ኢትዮጵያን ከሩዋንዳ በመቀጠል በወረርሽኝ ወቅት የክትባት ሙከራ ጥናት ሁለተኛ ሀገር ለመሆን ያስቻላትን ስኬት የሚያስቀጥሉ የምርምር ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።


 

የክሊኒካል ሙከራው ዓለም አቀፍ ወረርሽኞችን መከላከልና ምላሽ መስጠት የሚያስችል ልምድ ተገኝቶበታል ያሉት ደግሞ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለምሰገድ አብዲሳ ናቸው።


 

በወረርሽኝ ዝግጁነትና ፈጠራ ጥምረት (CEPI) የዝግጁነትና ምላሽ ዳይሬክተር ዶክተር ኒኮል ሉሪ፤ በክሊኒካል ሙከራው የተገኘው መረጃ ለሕብረተሰብ ጤና አደጋ ምላሽ እገዛ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም