ቀጥታ፡

የአሁኑ ትውልድ ፈጠራና ክህሎትን በማበልፀግ ከቅድመ አያቶች የተረከባትን ሀገር ዕድገት ማፋጠን ይጠበቅበታል

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 26/2018 (ኢዜአ)፦የአሁኑ ትውልድ ፈጠራና ክህሎትን በማበልፀግ ከቅድመ አያቶች የተረከባትን ሀገር ዕድገት ማፋጠን እንደሚጠበቅበት አባትና እናት አርበኞች ገለጹ።

በቀደምት ጀግኖች አርበኞች ታላቅ ተጋድሎ የተረከቧትን ኢትዮጵያ ዕድገትና ብልፅግና ለማረጋገጥ በትጋት እንደሚሰሩም የአዲስ አበባ ወጣቶች ተናግረዋል።

በ1928 ዓ.ም የፋሽስት ጣሊያን ጦር ኢትዮጵያን በግፍ ከወረረ በኋላም የኢትዮጵያ አርበኞች በየጫካውና በየበረሃው ለአምስት ዓመታት ባደረጉት አኩሪ ተጋድሎ ድልን ተቀዳጅተዋል።

ሚያዚያ 27ም የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት፣ ጀግንነትና ነፃነት ለዓለም የተበሰረበት ታሪካዊ የድል ቀን በመሆን የአሁኑ ትውልድ የነፃነት ተምሳሌት ሀገር እንዲረከብ አስችሎታል።

የኢትዮጵያ ጀግኖች በጣሊያን ወራሪ ኃይል የተቀዳጁትን ድል ለማስታወስ በየዓመቱ ሚያዚያ 27 ቀን የሚከበረው ''የአርበኞች ድል በዓል'' ዘንድሮም ለ85ኛ ጊዜ ነገ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ይከበራል።

ለዚህም ጀግኖች አርበኞች የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ክብር በማስጠበቅ የከፈሉትን ውድ ዋጋ ክብር ለመስጠት ከማለዳው 12፡00 ሰዓት ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት 21 ጊዜ መድፍ እንደሚተኮስ አስታውቋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው አባትና እናት አርበኞች ፤ ኢትዮጵያ በቀደምት አርበኞች አኩሪ ተጋድሎ ሉዓላዊ ነፃነቷን አስከብራ የመጣች ሀገር ናት ብለዋል።

አባት አርበኛ አለምነው አያሌው እንዳሉት፤ የአሁኑ ትውልድ ፈጠራና ልማትን በማፋጠን ከቅድመ አያቶች የተረከቧትን ሀገር ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።

ተተኪ እናት አርበኛ ሰብለ ንጋቱ በበኩላቸው፤ ቀደምት ጀግኖች ነፃነቷን ያስጠበቋት ሀገር ዕድገትና ብልፅግና ለማፋጠን የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ዕድገትና ብልፅግና በማረጋገጥ የቅድመ አያቶችን የታሪክ አደራ መወጣት እንዳለበት የተናገሩት ደግሞ አባት አርበኛ ሃምሳ አለቃ ዲባባ ጫላ ናቸው ፡፡

የአዲስ አበባ ወጣቶች በበኩላቸው እንዳሉት፤ ቀደምት አያቶች በጣሊያን ፋሺስት ወራሪ ኃይል ላይ የተቀዳጁት አኩሪ ድል ከቅኝ ግዛት ነፃ የሆነችና የነጻነት ቀንዲል የሆነች ኢትዮጵያን እንድንረከብ አስችሎናል።

በዚህም ጀግኖች አርበኞች ለዓለም ጭቁን ህዝቦች የነፃነት ተምሳሌት ኢትዮጵያን ለትውልድ ማሻገር እንደቻሉት ሁሉ እኛ ወጣቶችም ሁለንተናዊ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በትጋት እንሰራለን ብለዋል።

ቀደምት አርበኞች ለኢትዮጵያ ነፃነት የከፈሉት መስዋዕትነት ለሀገር እድገትና ልማት እንዲሁም ሉአላዊነት መከበር ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን  ገልጸዋል።

ከመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል አብዲ መካ፤ ቅድመ አያቶች የተቀዳጁትን አኩሪ የድል ታሪክ አሁን በዕድገቷና በልማቷ  መድገም  አለብን ብሏል።

የኢትዮጵያን ዕድገት ለማስቀጠል በተሰማራበት የሥራ መስክ ሁሉ በትጋት እንደሚሰራ አረጋግጧል።

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ የተመኝ አስማማው በበኩሏ፤ የኢትዮጵያን ልማትና ዕድገት ማፋጠን የቀደምት አርበኞችን የድል ታሪክ ማፅናት መሆኑን ገልፃለች።

የኢትዮጵያ የዕድገትና ብልፅግና ጉዞ ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን የሚያረጋግጥ ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ነው ያለው ደግሞ ወጣት  ፋሲል አሳምነው ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም