ቀጥታ፡

ቼልሲ ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ውጪ ሆነ 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ35ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ኖቲንግሃም ፎረስት ቼልሲን 3 ለ 1 አሸንፏል።

በስታምፎርድ ብሪጅ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ታይዎ አዎኒዪ ሁለት ግቦችን ሲያስቆጥር  ኢጎር ጄሱስ ቀሪዋን ጎል ከመረብ ላይ አሳርፏል። 

ጆአኦ ፔድሮ ለቼልሲ ብቸኛውን ግብ በግሩም ሁኔታ በመቀስ ምት አስቆጥሯል። 

የቼልሲው ኮል ፓልመር በመጀመሪያው አጋማሽ ፍጹም ቅጣት ምት ስቷል። 

በሊጉ 13ኛ ሽንፈቱን ያስተናገደው ቼልሲ በ48 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል። ይህን ተከትሎም ከአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ውጪ መሆኑ ተረጋግጧል። 

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ቀሪ ሶስት ጨዋታዎቹን ቢያሸንፍ እንኳ 58 ነጥብ ካላቸው ሊቨርፑል እና አስቶንቪላ ጋር እኩል መሆን ስለማይችል፣ በቀጣዩ የውድድር ዘመን በአውሮፓ መድረክ አይሳተፍም።

ቼልሲ ባለፉት ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ተሸንፏል። 

በአንጻሩ በሊጉ 11ኛ ድሉን ያስመዘገበው ኖቲንግሃም ፎረስት በ42 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። ላለመውረድ በሚያደርገው ትግል ወሳኝ ሶስት ነጥብ አሳክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም