ቀጥታ፡

በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው መቻል ነጥብ ሲጥል ሃዋሳ እና ሸገር ከተማ  አቻ ተለያይተዋል 

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ30ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዋል።

በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ መቻል እና አዳማ ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ውጤቱን ተከትሎ መቻል በ48 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አምስት ዝቅ የማድረግ እድል አልተጠቀመበትም።

አዳማ ከተማ በ35 ነጥብ ደረጃውን ከ16ኛ ወደ 14ኛ ከፍ አድርጓል። 

ባለፉት ዘጠኝ የሊጉ ጨዋታዎች ከድል የራቀው አዳማ ከተማ በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ሌላኛው መርሐ ግብር ሃዋሳ ከተማ እና ሸገር ከተማ አንድ አቻ ተለያይተዋል።


 

ብሩክ ታደለ በ43ኛ ደቂቃ ከመረብ ላይ ባሳረፋት ጎል ሃዋሳ ከተማ መሪ ሆኗል። 

ይስሃቅ ገብረኢየሱስ በ87ኛው ደቂቃ ለሸገር ከተማ ያስቆጠረው ግብ ለሸገር ከተማ አንድ ነጥብ አስገኝቷል። 

ሃዋሳ ከተማ በ44 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ከድል ርቋል።

ሸገር ከተማ ደግሞ በ37 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃን ይዟል።  ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም።

ዛሬ በተደረገ የ30ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ወላይታ ድቻ ሀዲያ ሆሳዕና 1 ለ 0 አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም