ቀጥታ፡

የቴክኖሎጂ ፈጠራ ኹነቶች ለገበያ ትስስርና ለፈጠራ ስራዎች መስፋፋት ጉልህ ሚና አላቸው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2018(ኢዜአ)፦ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ኹነቶች የፈጠራ ስራዎች በስፋት እንዲተዋወቁና ምቹ የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ትልቅ መደላድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን በከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ተሳታፊዎች ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ "የቴክኖሎጂ ልህቀት ለሀገር ብልፅግና" በሚል መሪ ሐሳብ 16ኛውን ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት በማካሄድ ላይ ይገኛል። 

በዚህ አውደርዕይ ላይ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ተሳታፊዎቹም የኹነቱን አስፈላጊነት መስክረዋል።

ከምርታማነት ማሻሻያ እና የልህቀት ማዕከል የመጣው አንዷለም እንዲሪያስ፣ በባህላዊ መንገድ የሚሰራውን የወርቅ ማጣራት ስራ ወደ ዘመናዊ ለመቀየር ያለመ የፈጠራ ውጤት ይዞ መቅረቡን ተናግሯል፡፡ 


 

በባህላዊ መንገድ የሚሰራውን ወርቅ የማጣራት ስራ ወደ ዘመናዊ መቀየርን ዓላማ በማድረግ ቴክኖሎጂውን መስራት መቻሉን ተናግሯል፡፡

ከተግበረዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የመጣችው ዘርትሁን በየነ በበኩሏ፣ ከኮንስትራክሽን አካባቢዎች ወደ ከተማ የሚገቡ መኪናዎችን ንጽህና መጠበቅ የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይዛ መቅረቧን አስረድታለች፡፡  

ይህ ፈጠራ የከተማን ንጽህና ለመጠበቅ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም አስረድታለች።

ይህ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት የፈጠራ ባለቤቶች ስራዎቻቸውን ለተጠቃሚውና ለገበያ እንዲያቀርቡ ከማገዙ ባለፈ፣ ለሀገር ብልፅግና የቴክኖሎጂ ልህቀት ያለውን ፋይዳ በተግባር እያሳየ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ 

በ16ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት ላይ ከተሳተፉት መካከል ኢብራሂም ነጋሽ አንዱ ሲሆን፣ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ይዞ መቅረቡን አስረድቷል፡፡ 


 

እነዚህን ማሽኖች በሀገር ውስጥ ማምረት መቻሉ፣ ስፖርታዊ ቁሳቁሶችን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ከማስቀረት አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስገንዝቧል።

ከኤኤል ጂ ኮይካ ቲቬኤት ኮሌጅ የመጣችው ቤተልሄም ደርጉ፣ የዶሮ እርባታን ሳይንሳዊና ጤናማ በሆነ መንገድ ለማከናወን የሚያስችል የፈጠራ ስራ ማቅረባቸውን ገልጻለች። 


 

ይህ ቴክኖሎጂ በተለይ ለዶሮዎቹ ተስማሚና ንፁህ አካባቢን በመፍጠር ረገድ ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም አብራርታለች።

የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለቤቶቹ ለሥራቸው ስኬት መሰል አውደ-ርዕዮች ትልቅ ፋይዳ እንዳላቸው አብራርተዋል፡፡

ዘርትሁን በየነ እንደገለጸችው፣ በከተማው አስተዳደርና በየኮሌጆቹ በኩል ከግብዓት አቅርቦት ጀምሮ የሚደረጉ ሁለንተናዊ ድጋፎች የፈጠራ ሥራዎቻቸው ውጤታማና ፍሬያማ እንዲሆኑ ትልቅ አቅም እንደፈጠሩላቸው ገልጻለች፡፡

ኢብራሂም ነጋሽ በበኩሉ፣ እንደነዚህ ያሉ መድረኮች በየጊዜው መዘጋጀታቸው የፈጠራ ባለቤቶች ሥራዎቻቸውን ለሕዝብ እንዲያስተዋውቁ ከማድረጉም ባለፈ፣ ዘላቂ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ምቹ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጿል።

የፈጠራ ሥራዎችን ለዕይታ የሚያበቁ መድረኮች መኖራቸው ለበለጠ ሥራ የሚያነሳሳ መሆኑን በመጥቀስ፤ ተማሪዎች በቴክኖሎጂና በፈጠራ ዘርፍ ላይ በንቃት በመሳተፍ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ ያቀረበችው ደግሞ ቤተልሄም ደርጉ ናት፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም