የአፍሪካ የዓለም ቅርስ ቀን በመልካ ቁንጡሬ ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካ የዓለም ቅርስ ቀን በመልካ ቁንጡሬ ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር፣ የአፍሪካ የዓለም ቅርስ ቀንን ሚያዝያ 28/2018 ዓ.ም በመልካ ቁንጡሬ አርኪዮሎጂ ሳይት እንደሚከበር አስታወቀ።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ10ኛ ጊዜ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ4ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዘንድሮውን ቀን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ህይወት ኃይሉ እና የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደራራ ከተማ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ህይወት ኃይሉ በመግለጫቸው፤ የቀኑ መከበር ኢትዮጵያ በቅርስ ጥበቃና በቱሪዝም ዘርፍ እያከናወነች የምትገኘውን ተግባር ለዓለም ለማሳየት ይጠቅማል ብለዋል፡፡
ቅርሶችን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማቆየት የሚደረገውን ጥረትም እንደሚያነቃቃ ተናግረዋል፡፡
በተለይም በዩኔስኮ (UNESCO) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበውን የመልካ ቁንጡሬና ባልጪት አርኪዮሎጂ ሳይትን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የአፍሪካና የኢትዮጵያ ቅርሶች ያላቸውን ሁለንተናዊ ፋይዳ በማስተዋወቅ፣ ለቅርሶች ጥበቃና እንክብካቤ የሚደረገውን ሕዝባዊ ተሳትፎ ለማሳደግና ቅርሶች ለኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እድገት ያላቸውን ሚና ለማሳየት እንደሚረዳም ተናግረዋል፡፡
የኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ደራራ ከተማ በበኩላቸው፤ ዘንድሮ የቀኑ ማዕከል የሆነው መልካ ቁንጡሬ የሰው ልጅ ቀደምት የድንጋይ መሣሪያዎች አጠቃቀምና የአኗኗር ዘይቤን የሚያሳዩ በርካታ የቅሪተ-አካል መገኛ መሆኑን አብራርተዋል።
መካነ-ቅርሱ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ ቢሮው በትኩረት እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ በክልሉ የሚገኙ የተለያዩ ቅርሶች እንዲተዋወቁና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ እየተሠራ እንደሚገኝም አመልክተዋል።
ሚያዝያ 28 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው በዚህ ስነስርዓት ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የአርኪዮሎጂ ባለሙያዎችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።