ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የቱሪዝም ጸጋዎቿን እንድትጠቀም የግል ዘርፉ የሆቴልና የመዳረሻ ልማት ወሳኝ ነው

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን የቱሪዝም ጸጋዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የግል ዘርፉ በሆቴልና በመዳረሻ ልማት ላይ የሚኖረው ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሕር ዳር ታሪኳን ሳትለቅ ዘመኑን እየዋጀች መሆኑን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ቀደም ሲል የከተማዋ ትዝታ በነበረው በታሪካዊው ጣና ሆቴል ሥፍራ ዓለም አቀፍ ደረጃን ያሟላ የፎር ፖይንትስ ባይ ሸራተን (Four Points by Sheraton) ሆቴል የግንባታ ፕሮጀክት በይፋ መጀመሩን አመልክተዋል።


 

በሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሚገነባው ይህ የሆቴል ፕሮጀክት ከተማዋን የቱሪዝም ሠገነት እንደሚያደርጋት ተናግረዋል።

በርካታ አገልግሎቶችን አሟልቶ በአሥራ ስምንት ወራት ግንባታው የሚጠናቀቀው ይህ ሆቴል፣ የግል ባለ ሀብቱ በሀገሪቱ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ውስጥ ያለውን ሚና በተግባር የሚያሳይ ነው ብለዋል።


 

ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ በተለያዩ ዘርፎች እያመጣ ያለው ለውጥ የሚደነቅ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ይህ የሆቴል ግንባታም ለባሕር ዳር በጸጋ ላይ ጸጋ የሚጨምር መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ፕሮጀክቱን በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት ለከተማዋና ለሀገሪቱ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም