በከተማዋ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በከተማዋ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ነው
ደሴ፣ሚያዚያ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በከተማዋ የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ሰፊ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ ገለጹ፡።
በከተማ አስተዳደሩ በመኖሪያ ቤት ማህበር ለተደራጁ 96 ማህበራት የጋራ መኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ርክክብ ተደርጓል።
የከተማው ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ እንደገለጹት፣ በከተማው የነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
በዛሬው እለትም በ96 ማህበራት ለተደራጁ 6 ሺህ 438 ዜጎች የጋራ መኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ ርክክብ መፈጸሙን ገልፀዋል።
በዚህም በማህበር ለተደራጁ የቤት ፈላጊዎች የጋራ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ከተማ አስተዳደሩ 117 ሄክታር መሬት በማዘጋጀት ለአንድ ማህበር 1 ሺህ 500 ካሬ ሜትር ቦታ ማስረከቡን ተናግረዋል።
በዚህም ባለአንድ መኝታ መኖሪያ ቤት ለሚገነቡ አራት ማህበራት፣ ባለሁለት መኝታ ለሚገነቡ 56 ማህበራት እንዲሁም ባለሦስት መኝታ ለሚገነቡ 36 ማህበራት የግንባታ ቦታ ተሰጥቷል ብለዋል።
የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ደረጃቸውን ጠብቀው እንዲገነቡ ከተማ አስተዳደሩ ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋል ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ መሰረተ ልማት የማሟላት ሥራም በትኩረት ይከናወናል ብለዋል።
ዛሬ የተረከቡት የቤት መስሪያ ቦታ ለረጅም ጊዜ ጥያቄያችው ምላሽ የሰጠ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የዕድሉ ተጠቃሚ አቶ እሸቱ ካሳሁን ናቸው።
የቤቱ ግንባታ በተቀመጠው ዲዛይን መሰረት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ የመኖሪያ ቤት ችግራቸው እንዲፈታ የሚጠበቅባቸውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።
ሌላዋ የዕድሉ ተጠቃሚ ወይዘሮ ሰሚራ አህመድ በሰጡት አስተያየት የመኖሪያ ቤት ችግር ጫና ፈጥሮባቸው መቆየቱን ተናግረዋል።
ለአስተዳደሩ ሲያቀርቡ የነበረው የቤት መስሪያ ቦታ ጥያቄ በአሁኑ ወቅት ምላሽ በማግኘቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በቦታ ርክክብ ሥነ ስርዓቱ ላይ የአማራ ክልል እና የደሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።