በዞኑ ሰላምን በማጽናት የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ሰላምን በማጽናት የማህበረሰቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ይጠናከራሉ
ደብረ ማርቆስ፣ሚያዚያ 26/2018 (ኢዜአ)፦በምስራቅ ጎጃም ዞን ሰላምን በማጽናት የማህበረሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ።
በዞኑ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ላይ የሚመክር መድረክ በደብረ ማርቆስ ከተማ ተካሄዷል።
በመድረኩም የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኑርልኝ ብርሃኑ እንዳሉት፤ በበጀት ዓመቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ሰላምን በማስፈን ለልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት ረገድ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።
በቀሪ ወራትም ተጨማሪ ስራዎችን በማከናወን የበለጠ ስኬት ለማስመዝገብ ርብርብ እንደሚደረግ ጠቅሰው፤ መድረኩም በስራ አፈፃፀም የታዩ ጥንካሬዎችን በማስቀጠል ድክመቶችን ለማረም ታሳቢ ያደረገ ነው ብለዋል።
የዞኑ ሰላምና ጸጥታ መምሪያ ሃላፊ አቶ ደምስ አለኸኝ በበኩላቸው፤ በዞኑ የሰፈነው ሰላም የተለያዩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማከናወን ማስቻሉን ጠቁመዋል።
በዞኑ የተጀመሩ የልማት ስራዎችን የማፋጠን ተግባር ህብረተሰቡን ባሳተፈ አግባብ እየተከናወነ ሲሆን ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም አረጋግጠዋል።
በዞኑ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ ለተሻሻሉ አሰራሮችና ቴክኖሎጂዎች ትኩረት መሰጠቱን ያነሱት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ጥላሁን ንጋቱ ናቸው።
በዚህም በ2017/18 የምርት ዘመን የሰብል ምርታማነትን በሄክታር ከ35 ወደ 38 ኩንታል ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል።
በመኸር ወቅቱ ከለማው ከ640 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ23 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ጠቅሰው፤ በመስኖ ልማቱም እስካሁን ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተገኝቷል ብለዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት የግብርና፣ የአካባቢ ጥበቃ እና ውሃ ስራዎች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ከፍያለው ሙላቴ፤ በልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እንዲጠናከሩ አሳስበዋል።