ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር በአካልና በአእምሮ የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመገንባት ጉልህ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፣ሚያዚያ 26/2018 (ኢዜአ)፦የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የእናቶችና ሕፃናትን የተመጣጠነ የምግብ አቅርቦት በማሟላት፣ በአካልና በአእምሮ የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር ገንቢ ሚና እንዳለው የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የአዳም ፋውንዴሽን መሥራችና ሊቀ-መንበር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብርን ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ማስጀመራቸው ይታወቃል፡፡

በመርሐ ግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኢትዮጵያ በስንዴ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራና በሌሎች ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች ላይ ያገኘችው ለውጥ በሌማት ትሩፋት ሥራም ይደገማል ብለዋል፡፡

ሌማት ከማዕድ ማስቀመጫና ማቅረቢያ መሶብ ባለፈ የሕብስት መትረፍረፍን፣ በአምራቾችና ሸማቾች መካከል መቀራረብንና የፍላጎት መጣጣምን እንደሚያረጋግጥ ገልጸዋል፡፡ 

የሌማት ትሩፋት ሰዎች ለተሟላ አካላዊ ጤንነትና አእምሯዊ ብስለት ምግብን በዓይነትና በመጠን እንዲያገኙ በማድረግ ሉዓላዊነትና ራስን የመቻል ነፃነትን ያውጃል ብለዋል፡፡ 

የሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር ከተትረፈረፈ ማዕድ እስከ ሀገር ድረስ የተዘረጋ፣ መቀንጨርን ጨርሶ ለማጥፋት ያለንን አቅም መጠቀም እንደምንችል የሚያሳይ ኢኒሼቲቭ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የአዳም ፋውንዴሽን መሥራችና ሊቀ-መንበር አቶ ደመቀ መኮንን ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ትብብር፣ ፈጠራ፣ ልህቀት፣ አካታችነት እና በሕፃናት ላይ ማተኮር የአዳም ፋውንዴሽን የተመሠረተባቸው መሠረታዊ እሴቶች ናቸው፡፡ 

በኢትዮጵያ በሌማት ትሩፋት መርሐ ግብር የሚከናወኑ ተግባራት ተስፋ ሰጭ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን ጠቅሰው፣ ፋውንዴሽኑ ከመንግሥትና ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡

በአካልና በአእምሮ የበለጸገ አምራችና ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት፣ እንዲሁም በራሱ የሚተማመን ዜጋ ለመፍጠር ሥርዓተ-ምግብ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

የሰው ልጅ የበለጸገ አእምሮ ፈጠራ የሚከናወነው 80 በመቶው ከጽንስ ጀምሮ ባሉ ሁለት ዓመታት ውስጥ መሆኑን ገልጸው፤ በዚያ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚገባ ያስገነዝባል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተመጣጠነ ምግብ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ መንግሥት ጥሩ ጅምሮችን አሳይቷል ያሉት አቶ ደመቀ፤ ለስኬቱ በጋራ ርብርብ ውስጣዊ አቅምን አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ግልጽ የምግብና የተመጣጠነ ምግብ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ነው ያሉት አቶ ደመቀ፤ ይህም በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ የሥርዓተ-ምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡ 

የአዳም ፋውንዴሽን እንደ ጤና ጥበቃ፣ ግብርናና መሰል ቁልፍ የመንግሥት ተቋማት ጋር በቅርበት እንደሚሠራ ገልጸው፤ የለማ አእምሮ ለመፍጠር ከአጋር አካላት ጋርም በትብብር እንሠራለን ብለዋል፡፡

የአዳም ፋውንዴሽን በአፍሪካ መቀንጨርን በመግታት "አጀንዳ 2063" ግቡን እንዲመታ ለማገዝ በቀድሞው የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የተመሠረተ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር በመተባበር የተመጣጠነ ምግብን ተደራሽ በማድረግ በአፍሪካ መቀንጨርን የማስቆም ዓላማን አንግቦ፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን በቁጥር 7260 ተመዝግቦ ሥራ ከጀመረ ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም