ቀጥታ፡

ማዕከሉ በሰመራና አካባቢው ለእናቶችና ህፃናት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ ያግዛል

ሰመራ፣ሚያዚያ 26/2018 (ኢዜአ)፦በሰመራ ከተማ በሚገኘው ጤና ጣቢያ የተገነባው የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ማዕከል አገልግሎት መጀመር በሰመራና አካባቢው ለእናቶችና ህፃናት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት የተሻለ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ ተናገሩ።

በሰመራ ከተማ በሚገኘው ጤና ጣቢያ የተገነባው አዲስ የእናቶችና ሕፃናት ሕክምና ማዕከል፣ ከፍተኛ የመንግስት ሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዛሬው ዕለት ተመረቀ። 

በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኀላፊ አቶ ያሲን ሐቢብ እንዳሉት፤ የማዕከሉ ስራ መጀመር በከተማውና አካባቢው የተሻሻለ የጤና አገልግሎት ለመስጠት ፋይዳው የጎላ ነው።


 

ማዕከሉ በጤና ጣቢያው የነበረውን የአገልግሎት መጨናነቅና የስራ ጫና ያቃልላል ያሉት ሃላፊው፤ በተለይም በከተማዋና በአካባቢው ለሚገኙ እናቶችና ሕፃናት የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነት ይበልጥ ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል።

እናቶች ለህክምና ልጆቻቸውን በመያዝ ወደ ዱብቲና ሎጊያ የሚያደርጉትን ጉዞ የሚያስቀርላቸው መሆኑንም አንስተዋል።

በክልሉ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ እየተከናወኑ ላሉት ተግባራት አንዱ ማሳያ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

በምረቃው ላይ የተገኙት የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዱ ሙሳ፣ በፍጥነት እያደገች ለምትገኘው ከተማ የማዕከሉ ሥራ መጀመር ወሳኝ መሆኑንና እናቶች ሳይጉላሉ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በተለይም የእናቶችን ተጨማሪ ወጪና እንግልትን ያስቀረ መሆኑን ገልፀው ለዚህ ውጤት መሳካት ቢሮውን አመስግነዋል።

ለማዕከሉ ግንባታ 10 ሚሊየን ብር ወጪ መደረጉም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም