ቀጥታ፡

የኮሪደር ልማቱ ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት መስፋፋት ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል

ባሕር ዳር፤ ሚያዝያ 26/2018 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለቱሪዝምና ኢንቨስትመንት ዘርፉ መስፋፋት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ገለፀ።

የቢሮው ኃላፊ ሞላ መልካሙ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኮሪደር ልማቱ የተጎሳቆሉ ከተሞችን በማልማት ውበታቸው እንዲወጣ አድርጓል።

የከተሞችን የኮንስትራክሽን ዘርፍ ከማነቃቃት ባለፈ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸው እንዲነቃቃ ማስቻሉንም ጠቁመዋል።

ከተሞች ለነዋሪዎች የተመቹ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸው፤ ለቱሪዝም ዘርፉ ማደግና የከተሞችን የኢንቨስትመንት ፍሰት በማሳለጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም አንስተዋል። 

በያዝነው ዓመት በ106 ሔክታር ላይ የኮሪደር ልማት ለመሥራት መታቀዱን እና እስካሁን በ80 ሔክታሩ ላይ መከናወኑን አረጋግጠዋል።

በዚህ ሥራም የተሽከርካሪና የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 108 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልማት መከናወኑን አስታውቀዋል።

በተሠራው የኮሪደር ልማት 10 የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ 168 ደረጃቸውን የጠበቁ ካፍቴሪያዎች፣ የሕጻናት መዝናኛዎች፣ የአረጋውያን ማረፊያዎችና ሌሎች ማኅበራዊ አገልግሎት ሰጪ ስፍራዎች መካተታቸውን አብራርተዋል።

ለኮሪደር ልማቱ ከ6 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልጸው፤ ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮኑ ሕብረተሰቡ በገንዘብ፣ በጉልበቱና ቁሳቁስ ተሳትፎ ያደረገበት መሆኑን አስገንዝበዋል።

በኮሪደር ልማቱ ለ112 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠሩንም አመላክተዋል።

በቀጣይ ልማቱን ወደ ሌሎች ከተሞች የማስፋቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ነው ያመላከቱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም