በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በአሲድ የተጠቃ መሬትን በኖራ በማከም የሰብል ምርታማነትን ለማሳድግ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በአሲድ የተጠቃ መሬትን በኖራ በማከም የሰብል ምርታማነትን ለማሳድግ እየተሰራ ነው
ጎንደር፤ሚያዚያ 26/2018(ኢዜአ)፦በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በመጪው የመኸር ወቅት ከ12ሺህ ሄክታር በላይ በአሲድ የተጠቃ መሬትን በኖራ በማከም የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው ሃላፊ አቶ ንጉሴ ማለደ ለኢዜአ እንደገለጹት የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ ከተቀመጡ ስትራቴጂዎች አንዱ አሲዳማ የእርሻ መሬትን በኖራ ማከም ነው፡፡
በዚህም በመኸር ወቅት ሙሉ በሙሉ እና በከፊል በአሲድ ተጠቅተው ምርት መስጠት ያቆሙ የእርሻ መሬቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማከም የሰብል ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በእስካሁኑ ጥረት ከ7 ሺህ ኩንታል በላይ ኖራ በመርጨት 8 ሺህ ሄክታር መሬት ለማከም መቻሉን ገልጸው፣በቀሪ ወራትም ተጨማሪ የእርሻ መሬት ለማከም ሥራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
አቶ ንጉሴ እንዳሉት፥ ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ እንደታየው በኖራ ከታከመ መሬት በሄክታር እስከ 15 ኩንታል የምርት ጭማሪ ለማግኘት ተችሏል።