ቀጥታ፡

ለሀገር ግንባታ የሚፈጥሩ አዕምሮዎችና የሚሠሩ እጆች ዋነኛ ምሰሶዎች ናቸው-ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 25/2018 (ኢዜአ)፦ለሀገር ግንባታ የሚፈጥሩ አዕምሮዎችና የሚሠሩ እጆች ዋነኛ ምሰሶዎች ናቸው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ የሥራና ክህሎት ቢሮ ያዘጋጀው 16ኛው ከተማ አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ሳምንት "የቴክኖሎጂ ልህቀት ለሀገር ብልፅግና" በሚል መሪ ሐሳብ በአራዳ ፓርክ ተከፍቷል።


 

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች በዚሁ ወቅት፤ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ኅብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (Artificial Intelligence) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው መሾማቸው ኢትዮጵያ በዘርፉ እያሳየች ያለችውን ትልቅ እመርታ ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

ሀገር በሚፈጥሩ አዕምሮዎችና በሚሠሩ እጆች ይገነባል ያሉት ከንቲባዋ፤ለዚህም የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች እያከናወኑ ላለው ተግባር ዕውቅና መስጠት እንደሚገባ ተናግረዋል።

ሀገር በልጆቿ ጥረት እንደምትገነባ ገልጸው፤በተለይም በቴክኖሎጂ ዘርፍ እየታየ ያለው ለውጥ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ለሀገር የኢኮኖሚ ዕድገትና ለኢንዱስትሪ ሽግግር መሠረት የሚጣልበት መሆኑንም ገልጸዋል።


 

ቀደም ሲል ከውጭ ሀገር በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ሲገቡ የቆዩ ምርቶች አሁን ላይ በሀገር ውስጥ በቴክኒክና ሙያ ተቋማት መመረት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም በከተማዋ እየተከናወኑ ያሉ ግዙፍ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የዘርፉ ባለሙያዎች ዕውቀታቸውና ጥበባቸው በተግባር እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። 

ምርቶቹን በሀገር ውስጥ ከመተካት ባለፈ ዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተወዳዳሪ በማድረግ ወደ ውጭ መላክ ላይ ትኩረት ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ይህ ሂደት ሀገራችን በራሷ አቅም እንድትቆም ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸው፤ የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን የፈጠራ ሥራዎች ለማስፋፋት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።


 

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአፍሪካ ኅብረት የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) እና የዲጂታል ጤና ዘርፍ መሪ (Champion) ሆነው መሾማቸው ይታወቃል። 

ሹመቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘርፉ ላሳዩት አመራርና ኢትዮጵያ በአህጉሪቷ የሰው ሠራሽ አስተውሎትንና የፈጠራ ሥራዎችን ለማስፋፋት እየተገበረች ላለው የላቀ ሚና የተሰጠ ዕውቅና መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።

ሹመቱ ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂን ሥነ ምግባራዊ መርሆች በተከተለ መልኩ በማልማት፣በመመራመር እንዲሁም ተግባራዊ በማድረግ በኩል ከአፍሪካ ቀዳሚዋ ሀገር እንድትሆን ለተሰሩ ሥራዎች ዕውቅና የሰጠ ነው በሚል መገለጹ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም