ቀጥታ፡

የግብርና ኢንሼቲቮችን በማስፋት ተረጂነትን ለመቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ሐረር፤ ሚያዝያ 26/2018 (ኢዜአ)፦ በግብርናው ዘርፍ የተጀመሩ ኢንሼቲቮችን በማስፋትና ምርታማነትን በማሳደግ ሕዝቡን ከተረጂነት የማላቀቅ ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሠ መሥተዳድር ሮዛ ኡመር ገለጹ።


 

ለእርሻ የሚውል ሁሉንም መሬት በማረስ ምርትና ምርታማነትን የማጎልበት ሥራ ተግባራዊ መደረጉን የገለጹት ወ/ሮ ሮዛ፤ የሚከናወኑ የግብርና ሥራዎችን ከዝናብ ጥገኝነት ለማላቀቅ የመስኖ ግድቦች ግንባታ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዚህም መሠረት አርሶ አደሩ የከርሰ ምድር ውኃን የፀሐይ ኃይል በመጠቀም አትክልትና ፍራፍሬ እንዲያለማ መደረጉን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በሌማት ትሩፋት ዘርፍ የሚገኘውን ምርታማነት ከማሳደግ አኳያም በወረዳዎች ሼዶችን በመገንባት ለወጣቶች እንዲተላለፍ መደረጉን እና ምርጥ ዝርያ ያላቸው የዶሮ ጫጩቶች ለአርሶ አደሩ መሠራጨታቸውን ገልጸዋል።

በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ረገድም ሥራዎች በየዓመቱ እያደጉ መምጣታቸውን ጠቅሰው፤ በዘንድሮው በጋ  በክልሉ አመርቂ የተፋሰስ ልማት ሥራ መከናወኑን አስታውቀዋል።

በዚህም ተረጂ የነበሩ አርሶ አደሮች ምርታማነትን በማጎልበት ከራሳቸው አልፈው ምርታቸውን ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም