የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 26/2018 (ኢዜአ)፡-የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማስፋት መጠነ-ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጌቱ ገረመው (ኢ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ አገልግሎቱ ፍትሐዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ባከናወነው ዘርፈ-ብዙ ሥራ ከዋናው ግሪድና ከግሪድ የራቁ በርካታ አዳዲስ አካባቢዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።
በበጀት ዓመቱ ያለፉት ዘጠኝ ወራት 103 አዲስ የገጠር ከተሞችና መንደሮች የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
ከነዚህ መካከልም 82ቱ ከዋናው የኤሌክትሪክ መረብ (ግሪድ) ቀሪዎቹ ደግሞ በፀሐይ ኃይል አማራጭ (ኦፍግሪድ) የተገናኙ ናቸው ብለዋል፡፡
ተደራሽነትን ከማስፋት አኳያም ባለፉት ዘጠኝ ወራት 423 ሺህ 200 አዲስ ደንበኞችን የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።
ከነዚህ መካከልም 31 ሺህ 298 ያህሉ አዲስ የኤሌክትሪክ ተደራሽ በሆኑት የገጠር ከተሞችና መንደሮች ተጠቃሚ የሆኑ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
አዲስ ኤሌክትሪክ ካገኙ ደንበኞች መካከልም 74 ነጥብ 2 ከመቶ የድኅረ ክፍያ እንዲሁም 25 ነጥብ 8 በመቶ የቅድመ ክፍያ ቆጣሪ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አስረድተዋል።