የሀገር ሽማግሌዎች በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገር ሽማግሌዎች በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናገሩ
ጎዴ፤ ሚያዝያ 26/2018 (ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እየተከናወነ ባለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በሸበሌ ዞን የጎዴ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ።
ልዩነቶችን በውይይት ለመፍታት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያከናወነ ያለው ተግባር የሚደገፍና ሰላማዊ የመፍትሔ ባህልን የሚያጠናክር መሆኑን የሀገር ሽማግሌ ሱልጣን ቃሊብ ሱልጣን ድእስ አብዲ አስረድተዋል።
የሀገር ሽማግሌ ሱልጣን አሊ አብዲ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ሰላም እንዲጸና እና በሀገሪቱ ብሔራዊ መግባባት እንዲጎለብት ኮሚሽኑ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት የሚበረታቱ መሆናቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከአጀንዳ ማሰባሰብ ጀምሮ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራት፤ ልዩነቶችን በምክክር በመፍታት ለተተኪው ትውልድ ምቹ ሀገርን ለመፍጠር ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም አስገንዝበዋል።
ኮሚሽኑ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያደርገውን ጥረት ማኅበረሰቡ በሰለጠነ መንገድ ሊጠቀምበት እንደሚገባ የመከሩት ደግሞ የሀገር ሽማግሌ ሱልጣን መህዲ ሁሴን ናቸው።
ልዩነቶችን በምክክር በመፍታት የሕዝብን አንድነት ለማጠናከር ሂደቱ ትልቅ ዕድል መሆኑን አስገንዝበው፤ ለዚህም እንደ ሀገር ሽማግሌ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።