የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 26/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ ሦስት መርሐ ግብሮች ጅማሮውን ያደርጋል።
ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ መቻል ከአዳማ ከተማ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቻል በ47 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዟል። ተጋጣሚው አዳማ ከተማ በ34 ነጥብ 16ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ29ኛ ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 1 ለ 0 ያሸነፈው መቻል፣ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ወደ ሜዳ ይገባል።
ቡድኑ ዛሬ የሚያሸንፍ ከሆነ ከሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በጊዜያዊነት ወደ አምስት ዝቅ ያደርጋል።
ባለፉት ስምንት የሊጉ ጨዋታዎች ከድል ጋር የተራራቀው አዳማ ከተማ ማሸነፍ ብቻ ሳይትሆን ከወራጅ ቀጠና ስፍራ በመጠኑም እንዲርቅ የሚያደርገው ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያስገኝለታል።
ከድል የራቀው አዳማ ከተማ በዛሬው ጨዋታ የሚቀዳጀው ድል የሦስት ነጥብ ጥማቱን ከመቁረጥ ባለፈ፣ ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ፈቀቅ እንዲል ትልቅ ዕድል ይሰጠዋል።
በሌላኛው መርሐ ግብር ሃዋሳ ከተማ ከሸገር ከተማ ከቀኑ 10 ሰዓት በአዲስ አበባ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ሃዋሳ ከተማ በ43 ነጥብ አራተኛ፣ ሸገር ከተማ ደግሞ በ36 ነጥብ ዘጠነኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ለስድስት ተከታታይ ጨዋታዎች ሶስት ነጥብ ያላገኘው ሃዋሳ ከተማ፣ ወደ ድል ለመመለስ ይጫወታል።
በ29ኛ ሳምንት ከወላይታ ድቻ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየው ሸገር ከተማ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።
ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ ከሀዲያ ሆሳዕና በአዲስ አበባ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ወላይታ ድቻ በ35 ነጥብ 11ኛ ደረጃን ይዟል። ሀዲያ ሆሳዕና በተመሳሳይ 35 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበልጦ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በ29ኛ ሳምንት ወላይታ ድቻ ከሸገር ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይቷል። ሀዲያ ሆሳዕና ባለፉት ሶስት ጨዋታዎች አቻ ወጥቷል።
ሁለቱም ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ይፋለማሉ።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 30ኛ ሳምንት መርሐ ግብር እስከ ሚያዚያ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ የሚዘልቅ ይሆናል።
ሲዳማ ቡና ሊጉን በ55 ነጥብ እየመራ ነው።
የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው በ14 ግቦች የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ዝርዝር በአንደኝነት ሲመራ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ በ10 ግቦች የቅርብ ተከታዩ በመሆን ይከተላል።